ሮሜ 9:1-21

ሮሜ 9:1-21 NASV

በክርስቶስ ሆኜ እውነት እናገራለሁ፤ አልዋሽም፤ ኅሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል። ታላቅ ሐዘንና የማያቋርጥ ጭንቀት በልቤ አለ። ለወገኖቼ ስል ስለ ወንድሞቼ እኔ ራሴ የተረገምሁና ከክርስቶስም ተለይቼ የተጣልሁ እንድሆን እንኳ እወድድ ነበር፤ እነርሱም የእስራኤል ሕዝብ ናቸው፤ ልጅ መሆን፣ መለኮታዊ ክብር፣ ኪዳን፣ ሕግን መቀበል፣ የቤተ መቅደስ ሥርዐትና ተስፋ የእነርሱ ናቸውና። አባቶችም የእነርሱ ናቸው፤ ክርስቶስም በሥጋ የትውልድ ሐረጉ የሚቈጠረው ከእነርሱ ነው፤ እርሱም፣ ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘላለም የተመሰገነ አምላክ ነው! አሜን። ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ተሽሯል ማለት አይደለም፤ ከእስራኤል የተወለደ ሁሉ እስራኤላዊ አይደለምና። ከአብርሃም ዘርም ስለ ሆኑ፣ ሁሉም ልጆቹ አይደሉም፤ ይልቁንስ፣ “ዘርህ በይሥሐቅ በኩል ይጠራልሃል” እንደ ተባለው ነው። ይህም ማለት የእግዚአብሔር ልጆች የተባሉት የሥጋ ልጆች አይደሉም፤ ነገር ግን የአብርሃም ልጆች የተባሉት የተስፋው ልጆች ናቸው። “ጊዜው ሲደርስ እመለሳለሁ፤ ሣራም ወንድ ልጅ ትወልዳለች” ተብሎ ተስፋው ተሰጥቷልና። ይህም ብቻ ሳይሆን፣ የርብቃ ልጆች አንድ አባት አላቸው፤ እርሱም አባታችን ይሥሐቅ ነው። መንትዮቹ ገና ሳይወለዱ፣ ወይም በጎም ሆነ ክፉ ሳያደርጉ፣ የእግዚአብሔር ሐሳብ በምርጫ ይጸና ዘንድ፣ በሥራ ሳይሆን ከጠሪው በመሆኑ፣ “ታላቁም ለታናሹ ይገዛል” ተብሎ ተነገራት። ይህም፣ “ያዕቆብን ወደድሁ፤ ዔሳውን ግን ጠላሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። እንግዲህ ምን እንላለን? በእግዚአብሔር ዘንድ ዐመፃ አለን? ፈጽሞ! ለሙሴ፣ “የምምረውን እምረዋለሁ፤ የምራራለትንም ራራለታለሁ” ይላልና። እንግዲህ ይህ ከሰው ፍላጎት ወይም ጥረት ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው። መጽሐፍ ፈርዖንን፣ “ኀይሌ በአንተ እንዲታይ፣ ስሜም በምድር ሁሉ እንዲታወቅ ለዚህ አስነሣሁህ” ይላልና። ስለዚህ እግዚአብሔር ሊምረው ለሚወድደው ምሕረት ያደርግለታል፤ ልቡ እንዲደነድን የፈለገውንም ያደነድነዋል። ከእናንተ አንዱ፣ “ታዲያ እንደዚህ ከሆነ እግዚአብሔር እስከ አሁን ለምን ይወቅሠናል? ምክንያቱም ፈቃዱን ሊቋቋም የሚችል ማን አለ?” ይለኝ ይሆናል። ነገር ግን ለእግዚአብሔር መልስ የምትሰጥ አንተ ማን ነህ? “ሥራ ሠሪውን፣ ‘ለምን እንዲህ ሠራኸኝ?’ ይለዋልን?” ሸክላ ሠሪ፣ ከሚሠራው ጭቃ፣ አንዳንዱን ሸክላ ለከበረ፣ ሌሎቹን ደግሞ ለተራ አገልግሎት የማድረግ መብት የለውምን?