የዮሐንስ ራእይ 6
6
የሰባቱ ማኅተሞች መከፈት
1ከዚህም በኋላ በጉ ከሰባቱ ማኅተሞች የመጀመሪያውን ሲከፍት አየሁ። ከአራቱ እንስሶች አንዱ እንደ ነጐድጓድ በሚያስገመግም ድምፅ “ና!” ሲል ሰማሁ። 2እነሆ ነጭ ፈረስ አየሁ፤ በፈረሱ ላይ የተቀመጠው ቀስት ይዞ ነበር፤ አክሊልም ተሰጠው፤ እርሱም ድል ነሺ ሆኖ ከድል ወደ ድል ለመሄድ ወጣ። #ዘካ. 1፥8፤ 6፥3፤6።
3በጉ ሁለተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ፥ ሁለተኛው እንስሳ “ና!” ሲል ሰማሁ። 4ሌላ ደማቅ ቀይ ፈረስ ወጣ፤ በፈረሱ ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር እንዲያስወግድና ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲተላለቁ ለማድረግ ሥልጣን ተሰጠው፤ ትልቅ ሰይፍም ተሰጠው። #ዘካ. 1፥8፤ 6፥2።
5በጉ ሦስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ ሦስተኛው እንስሳ “ና!” ሲል ሰማሁ፤ እነሆ ጥቊር ፈረስ አየሁ፤ በፈረሱ ላይ የተቀመጠው ሚዛን በእጁ ይዞ ነበር፤ #ዘካ. 6፥2፤6። 6ከአራቱ እንስሶች መካከል የመጣ የሚመስል ድምፅ ሰማሁ፤ ይህ ድምፅ “ግማሽ ኪሎ ያኽል ስንዴ የአንድ ቀን ደመወዝ፥ ለአንድ ኪሎ ተኩል ያኽል ገብስ ለአንድ ቀን ደመወዝ ይሁን፤ ዘይትንና ወይንን ግን አትጒዳ!” ሲል ሰማሁ።
7በጉ አራተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ የአራተኛውን እንስሳ ድምፅ “ና!” ሲል ሰማሁ፤ 8እነሆ ግራጫ ፈረስ አየሁ፤ በፈረሱ ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ይባል ነበር፤ ሲኦልም ይከተለው ነበር፤ ሞትና ሲኦልም የምድርን አንድ አራተኛ እጅ በጦርነት፥ በራብ፥ በቸነፈርና በምድር አራዊት እንዲገድሉ ሥልጣን ተሰጣቸው። #ሕዝ. 14፥21።
9አምስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ሰጡትም ምስክርነት የተገደሉትን ሰዎች ነፍሶች ከመሠዊያው በታች አየሁ፤ 10እነርሱ በታላቅ ድምፅ “ቅዱስና እውነተኛ፥ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፥ በምድር ባሉት ሰዎች ላይ የማትፈርደውና ስለ ደማችንም የማትበቀለው እስከ መቼ ነው!” እያሉ ጮኹ። 11ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፤ እንደ እነርሱ ገና የሚገደሉ፥ እንደእነርሱ አገልጋዮች የሆኑ የጓደኞቻቸውና የወንድሞቻቸው ቊጥር እስኪሞላ ድረስ ጥቂት ጊዜ ዐርፈው እንዲቈዩ ተነገራቸው።
12ከዚህ በኋላ በጉ ስድስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ ወደ እርሱ ተመለከትኩ፤ እነሆ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ፀሐይ እንደ ጥቊር የሐዘን ልብስ ጠቈረች፤ ጨረቃም በሙሉ እንደ ደም ቀላች፤ #ራዕ. 11፥13፤ 16፥18፤ ኢሳ. 13፥10፤ ኢዩ. 2፥10፤31፤ 3፥15፤ ማቴ. 24፥29፤ ማር. 13፥24-25፤ ሉቃ. 21፥25። 13በክረምት ወራት ብርቱ ነፋስ የበለስን ዛፍ ሲያወዛውዝ ፍሬው ከዛፉ ላይ እንደሚረግፍ የሰማይ ኮከቦችም ረገፉ። #ኢሳ. 34፥4። 14ሰማይም እንደ ብራና ተጠቅሎ ተወገደ፤ ተራራዎችና ደሴቶችም ሁሉ ከስፍራቸው ተወሰዱ። #ራዕ. 16፥20። 15የምድር ነገሥታት፥ ገዢዎች፥ የጦር አለቆች፥ ሀብታሞች፥ ኀይለኞች፥ አገልጋዮችና ጌቶችም ሁሉ በዋሻዎችና በተራራዎች አለቶች ውስጥ ተሸሸጉ፤ #ኢሳ. 2፥19-21። 16ተራራዎቹንና አለቶቹንም “ጋርዱን! በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ፊት፥ ከበጉም ቊጣ ሰውሩን! #ሆሴዕ 10፥8፤ ሉቃ. 23፥30። 17ታላቁ የቊጣ ቀን መጥቶአል፤ ማን ሊቋቋመው ይችላል?” አሉአቸው። #ኢዩ. 2፥11፤ ሚል. 3፥2።
Currently Selected:
የዮሐንስ ራእይ 6: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997