የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ራእይ 3

3
(5) የሰርዴስ ቤተ ክርስቲያን
1“ለሰርዴስ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤
“ይህ፥ ሰባቱን የእግዚአብሔር መንፈሶችና ሰባቱን ኮከቦች ከያዘው የተነገረ ነው፤ ሥራህን ዐውቃለሁ፤ በስም ሕያው ነህ፤ ነገር ግን ሞተሃል። 2ንቃ፤ ሊሞት የተቃረበውንና የቀረልህን ትንሽ ኀይል አጠናክር፤ በአምላኬ ፊት ሥራህን ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትም። 3እንግዲህ ምን ዐይነት ትምህርት እንደ ተቀበልክና እንደ ሰማህ አስታውስ፤ ጠብቀውም፤ ንስሓም ግባ፤ ባትነቃ ግን እንደ ሌባ በድንገት እመጣብሃለሁ፤ በምን ሰዓት ወደ አንተ እንደምመጣ አታውቅም። #ማቴ. 24፥43-44፤ ሉቃ. 12፥39-40፤ ራዕ. 16፥15። 4ነገር ግን ልብሳቸውን ያላረከሱ በሰርዴስ ጥቂት ሰዎች ከአንተ ጋር አሉ፤ እነርሱ ነጭ ልብስ መልበስ የሚገባቸው ስለ ሆኑ ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ። 5ድል የሚነሣ እንደ እነርሱ ነጭ ልብስ ይለብሳል፤ ስሙን በአባቴና በመላእክቱም ፊት አስታውቅለታለሁ፤ የሕያዋን ስም ከሚመዘገብበት ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስሰውም። #ዘፀ. 32፥32-33፤ መዝ. 69፥28፤ ራዕ. 20፥12፤ ማቴ. 10፥32፤ ሉቃ. 12፥8።
6“መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ!
(6) የፊላደልፍያ ቤተ ክርስቲያን
7“ለፊላደልፍያ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፤
“ይህ፥ ቅዱስና እውነተኛ ከሆነው፥ የዳዊት ቤት ቊልፍ ከያዘው የተነገረ ነው፤ እርሱ የሚከፍተውን ማንም አይዘጋውም፤ እርሱ የሚዘጋውንም ማንም አይከፍተውም። #ኢሳ. 22፥22፤ ኢዮብ 12፥14። 8ሥራህን ዐውቃለሁ፤ እነሆ፥ ማንም ሊዘጋው የማይችለውን የተከፈተ በር በፊትህ አድርጌልሃለሁ፤ ኀይልህ ትንሽ መሆኑን ዐውቃለሁ፤ ይሁን እንጂ ቃሌን ጠብቀሃል፤ ስሜንም አልካድክም። #ኢሳ. 49፥23፤ 60፥14፤ 43፥4። 9እንግዲህ፥ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን የሚሉትን እነዚያን ከሰይጣን ማኅበር የሆኑትን ውሸታሞች መጥተው በእግርህ ሥር እንዲወድቁ አደርጋቸዋለሁ፤ እኔ እንደ ወደድኩህም እንዲያውቁ አደርጋቸዋለሁ። 10ትዕግሥተኛ ሁን ያልኩህን ቃሌን ስለ ጠበቅህ እኔም በምድር ላይ የሚኖሩትን ሊፈትናቸው በዓለም ሁሉ ላይ ከሚመጣው ከመከራ ሰዓት እጠብቅሃለሁ። 11እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፤ አክሊልህን ማንም እንዳይወስድብህ ያለህን አጥብቀህ ያዝ። 12ድል የሚነሣውን በአምላኬ ቤተ መቅደስ ዐምድ አደርገዋለሁ፤ ከዚያም ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም በእርሱ ላይ እጽፋለሁ፤ ይህችም ከተማ ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደው አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ናት፤ የእኔንም አዲስ ስም በእርሱ ላይ እጽፋለሁ። #ራዕ. 21፥2፤ ኢሳ. 62፥2፤ 65፥15።
13“መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ!
(7) የሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን
14“ለሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦
“ይህ፥ አሜን ከሆነው፥ ታማኝና እውነተኛ ምስክር ከሆነው፥ የእግዚአብሔር ፍጥረት ሁሉ መገኛ ከሆነው የተነገረ ነው፤ #መሳ. 8፥22። 15ሥራህን ዐውቃለሁ፤ ቀዝቃዛ ወይም ትኩስ አይደለህም፤ ቀዝቃዛ ወይም ትኩስ ብትሆን ኖሮ መልካም በሆነ ነበር! 16ቀዝቃዛ ወይም ትኩስ ሳትሆን ለብ ያልክ ስለ ሆንክ ከአፌ አውጥቼ ልተፋህ ነው፤ 17‘እኔ ሀብታም ነኝ፤ ብዙ ሀብት አለኝ፤ የሚጐድለኝ ምንም የለም’ ትላለህ፤ ነገር ግን ጐስቋላ፥ ምስኪን፥ ድኻ፥ ዕውርና የተራቈትህ መሆንክን አታውቅም፤ 18ሀብታም ለመሆን በእሳት የተፈተነውን ወርቅ ከእኔ እንድትገዛ፥ የራቊትነትህን ኀፍረት ለመሸፈን ነጭ ልብስ እንድትለብስ፥ ለማየትም እንድችል የዐይን መድኃኒት ገዝተህ እንድትቀባ እመክርሃለሁ። 19እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ፤ እቀጣቸዋለሁም፤ ስለዚህ ትጋ፤ ንስሓም ግባ፤ #ምሳ. 3፥12፤ ዕብ. 12፥6። 20እነሆ! እኔ በበር ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ሰምቶ በሩን ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ ገብቼ ከእርሱ ጋር እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል፤ 21እኔ ድል ነሥቼ ከአባቴ ጋር በዙፋኑ ላይ እንደ ተቀመጥኩ እንዲሁም ድል የነሣ ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ።
22“መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያን የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ!”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ