የዮሐንስ ራእይ 4
4
የእግዚአብሔር ዙፋንና ሰማያዊው የጸሎት ሥነ ሥርዓት
1ከዚህ በኋላ ተመለከትኩ፤ እነሆ በሰማይ የተከፈተ በር ነበር፤
በመጀመሪያ ሰምቼው የነበረው እንደ እምቢልታ ያለው ድምፅ እንዲህ አለ፦ “ና ወደዚህ ውጣ፤ ወደፊት መሆን የሚገባቸውን ነገሮች አሳይሃለሁ፤” 2ወዲያውኑ በመንፈስ ተመሰጥሁ፤ እነሆ በሰማይ ዙፋን አየሁ፤ በዙፋኑም ላይ አንድ አካል ተቀምጦበት ነበር። 3በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ የነበረው መልኩ የኢያሰጲድንና የሰርዲኖን ዕንቊ ይመስል ነበር፤ በዙፋኑም ዙሪያ የመረግድ ዕንቊ የመሰለ ቀስተ ደመና ነበረ፤ #ሕዝ. 1፥26-28፤ 10፥1። 4እንዲሁም፥ በዙፋኑ ዙሪያ ኻያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፤ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ የለበሱና በራሳቸው ላይ የወርቅ አክሊል የደፉ ኻያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር። 5ከዙፋኑም መብረቅና ድምፅ ነጐድጓድም ይወጡ ነበር፤ በዙፋኑ ፊት የሚበሩ ሰባት ችቦዎች ነበሩ፤ እነርሱ ሰባቱ የእግዚአብሔር መንፈሶች ናቸው። #ዘፀ. 19፥16፤ ራዕ. 8፥5፤ 11፥19፤ 16፥18፤ ሕዝ. 1፥13፤ ራዕ. 1፥4፤ ዘካ. 4፥2። 6በዙፋኑ ፊት ጥርት ያለ የሚያንጸባርቅ የመስተዋት ባሕር ነበረ፤ በመካከል፥ በዙፋኑ ዙሪያ በስተፊትና በስተኋላ ብዙ ዐይኖች ያሉአቸው አራት እንስሶች ነበሩ። 7የመጀመሪያው እንስሳ አንበሳ ይመስል ነበር፤ ሁለተኛው በሬ ይመስል ነበር፤ ሦስተኛው የሰው ፊት የሚመስል ፊት ነበረው፤ አራተኛው የሚበር ንስር ይመስል ነበር። #ሕዝ. 1፥22፤ 10፥14። 8አራቱም እንስሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች ነበሩአቸው፤ በዙሪያቸውና በውስጣቸውም ዐይኖች ሞልተውባቸዋል፤ ሌሊትና ቀን፦
“ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ
ሁሉን የሚችል ጌታ አምላክ፥
የነበረ፥ ያለና የሚመጣውም”
ከማለት አያቋርጡም ነበር። #ሕዝ. 1፥18፤ 10፥12፤ ኢሳ. 6፥2-3።
9እንስሶቹ በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ለሚኖረው ገናናነት፥ ክብርና ምስጋና በሚያቀርቡበት ጊዜ ሁሉ፥ 10ኻያ አራቱ ሽማግሌዎች ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም በሚኖረው፥ በዙፋኑ ላይ በተቀመጠው ፊት በግንባራቸው ተደፍተው ይሰግዳሉ፤ አክሊሎቻቸውንም በዙፋኑ ፊት አኑረው፥ እንዲህ ይላሉ፦
11“ጌታችንና አምላካችን ሆይ፥
ሁሉን ነገር ስለ ፈጠርክ
ሁሉም ነገር የተፈጠረውና
የሚኖረው (ሕይወትን ያገኘው) በአንተ ፈቃድ ስለ ሆነ
ገናናነት፥ ክብርና ኀይልም ለአንተ ይገባል” ይሉ ነበር።
Currently Selected:
የዮሐንስ ራእይ 4: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997