የተናገረኝም መልአክ ከተማይቱንና ደጃፎችዋን፥ የግንቡንም አጥር የሚለካበት የወርቅ ዘንግ ነበረው፤ ከተማይቱም ርዝመትዋና ስፋትዋ እኩል የሆነ የአራት ማእዘን ቅርጽ ነበራት፤ መልአኩ ከተማይቱን በመለኪያው ዘንግ ለካትና ርዝመትዋ ሁለት ሺህ አራት መቶ ኪሎ ሜትር ያኽል ሆነ፤ ስፋትዋና ከፍታዋም ያንኑ ያኽል ሆነ፤ መልአኩ የግንቡን አጥር ለካ፤ መልአኩ በሚለካበት በታወቀው መለኪያ ልክ ሰባ ሁለት ሜትር ያኽል ሆነ፤ ግንቡም የተሠራው ከኢያሰጲድ ነበረ፤ ከተማይቱም እንደ መስተዋት በጠራ በንጹሕ ወርቅ የተሠራች ነበረች፤ የከተማይቱ ግንብ መሠረቶች በልዩ ልዩ የከበረ ድንጋይ ያጌጡ ነበሩ፤ የመጀመሪያው መሠረት ኢያሰጲድ ነበረ፤ ሁለተኛው ሰንፔር፥ ሦስተኛው ኬልቄዶን፥ አራተኛው መረግድ፥ አምስተኛው ሰርዶንክስ፥ ስድስተኛው ሰርድዮን፥ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፥ ስምንተኛው ቢረሌ፥ ዘጠነኛው ወራውሬ፤ ዐሥረኛው ክርስጵራስስ፥ ዐሥራ አንደኛው ያክንት፥ ዐሥራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበረ። ዐሥራ ሁለቱም ደጃፎች ዐሥራ ሁለት ዕንቆች ነበሩ፤ እያንዳንዱ ደጃፍ ከአንድ ዕንቊ የተሠራ ነበረ፤ የከተማይቱም መንገድ እንደ መስተዋት ብርሃን ከሚያስተላልፍ ከንጹሕ ወርቅ የተሠራ ነበረ። ሁሉን የሚችል ጌታ አምላክና በጉ የእርስዋ መቅደስ ስለ ሆኑ በከተማይቱ ውስጥ መቅደስ አላየሁም፤ የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላትና በጉ መብራትዋ ስለ ሆነ ከተማይቱ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጋትም። ሕዝቦች በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፤ የምድር ነገሥታትም ክብራቸውን ወደ እርስዋ ያመጣሉ፤ በዚያች ከተማ ሌሊት ስለሌለ ደጃፎችዋ በማንኛውም ቀን አይዘጉም። የመንግሥታት ገናናነትና ክብር ወደ እርስዋ ይገባሉ፤ ጸያፍ የሆነ ነገር ከቶ ወደ እርስዋ አይገባም፤ ርኲሰትን የሚያደርግና ውሸት የሚናገር ከቶ ወደ እርስዋ አይገባም፤ ወደ እርስዋ የሚገቡ ስሞቻቸው በበጉ የሕይወት መጽሐፍ የተጻፉ ብቻ ናቸው።
የዮሐንስ ራእይ 21 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ራእይ 21:15-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos