የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ራእይ 21:15-27

ራእይ 21:15-27 NASV

ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ የከተማዪቱን በሮች ቅጥር የሚለካበት የወርቅ ዘንግ ነበረው። ከተማዪቱም ርዝመቷና ስፋቷ እኩል ሆኖ አራት ማእዘን ነበረች። እርሱም ከተማዪቱን በዘንጉ ለካ፤ ርዝመቷም ዐሥራ ሁለት ሺሕ ምዕራፍ ሆነ፤ ስፋቷና ከፍታዋም እንዲሁ ሆነ። ደግሞም የከተማዪቱን ቅጥር ለካ፤ ርዝመቱም የመልአክ መለኪያ በሆነው በሰው መለኪያ መቶ አርባ አራት ክንድ ነበር። ቅጥሩ የተሠራው ከኢያሰጲድ ነበር፤ ከተማዪቱም እንደ መስተዋት ንጹሕ ከሆነ ወርቅ የተሠራች ነበረች። የከተማዪቱ ቅጥር መሠረቶች በሁሉም ዐይነት የከበረ ድንጋይ ያጌጡ ነበር፤ የመጀመሪያው መሠረት ኢያሰጲድ፣ ሁለተኛው ሰንፔር፣ ሦስተኛው ኬልቄዶን፣ አራተኛው መረግድ፣ አምስተኛው ሰርዶንክስ፣ ስድስተኛው ሰርድዮን፣ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፣ ስምንተኛው ቢረሌ፣ ዘጠነኛው ወራውሬ፣ ዐሥረኛው ክርስጵራስስ፣ ዐሥራ አንደኛው ያክንት፣ ዐሥራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበረ። ዐሥራ ሁለቱም በሮች ዐሥራ ሁለት ዕንቍዎች ነበሩ፤ እያንዳንዱም በር ከአንድ ዕንየተሠራ ነበረ። የከተማዪቱም አውራ መንገድ እንደ መስተዋት ብርሃን የሚያስተላልፍ ንጹሕ ወርቅ ነበረ። ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክና በጉ መቅደሷ ስለሆኑ፣ በከተማዪቱ ውስጥ ቤተ መቅደስ አላየሁም። የእግዚአብሔር ክብር ብርሃን ስለሚሰጣትና በጉም መብራቷ ስለሆነ፣ ከተማዋ ፀሓይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጋትም። ሕዝቦች በብርሃኗ ይመላለሳሉ፤ የምድር ነገሥታትም ክብራቸውን ወደ እርሷ ያመጣሉ። በዚያ ሌሊት ስለሌለ፣ በሮቿ በየትኛውም ቀን አይዘጉም። የሕዝቦች ግርማና ክብር ወደ እርሷ ይገባል። በበጉ የሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በስተቀር፣ ርኩሰትን የሚያደርግና ውሸትን የሚናገር ሁሉ አይገባባትም።