የዮሐንስ ራእይ 17
17
ታላቂቱ አመንዝራ ሴት
1ሰባቱን ጽዋዎች ይዘው ከነበሩት ከሰባቱ መላእክት አንዱ ወደ እኔ መጥቶ እንዲህ አለኝ፦ “ና! በብዙ ውሃዎች ላይ በተቀመጠችው በታላቂቱ አመንዝራ ሴት ላይ የሚደርሰውን ፍርድ አሳይሃለሁ፤ #ኤር. 51፥13። 2የምድር ነገሥታት ከእርስዋ ጋር አመንዝረዋል፤ የምድር ኗሪዎችም በአመንዝራነትዋ የወይን ጠጅ ሰክረዋል።” #ኢሳ. 23፥17፤ ኤር. 51፥7።
3ከዚህ በኋላ መልአኩ በመንፈስ ወደ በረሓ ወሰደኝ፤ በሁለንተናው የስድብ ስሞች በተጻፉት፥ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች ባሉት በቀይ አውሬ ላይ የተቀመጠች አንዲት ሴት አየሁ። #ራዕ. 13፥1። 4ሴቲቱ ሐምራዊና ቀይ ልብስ ለብሳ ነበር፤ በወርቅና በከበረ ድንጋይ በዕንቆችም አሸብርቃ ነበር፤ በእጅዋም የሚያጸይፍ ነገርና የአመንዝራነትዋ ርኲሰት የሞላበትን የወርቅ ጽዋ ይዛ ነበር። #ኤር. 51፥7። 5በግንባርዋም ላይ “የአመንዝሮችና የምድር ርኲሰቶች እናት፥ ታላቂቱ ባቢሎን” የሚል ምሥጢር ስም ተጽፎ ነበር። 6ያቺ ሴት በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ሰማዕታት ደም ሰክራ አየኋት፤ ባየኋትም ጊዜ እጅግ በጣም ተደነቅሁ። 7መልአኩ ግን እንዲህ አለኝ፤ “ስለምን ትደነቃለህ? የሴቲቱን ምሥጢርና እርስዋ የተቀመጠችበትን፥ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች ያሉትን፥ የአውሬውን ምሥጢር እገልጥልሃለሁ፤ 8ያየኸው አውሬ ቀድሞ ነበር፤ አሁን የለም፤ በኋላ ከጥልቁ ጒድጓድ ይወጣል፤ ወደ ጥፋቱም ይሄዳል፤ ዓለም ሲፈጠር ጀምሮ ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፉ የምድር ኗሪዎች፥ አውሬው ቀድሞ የነበረ፥ አሁን የሌለ፥ በኋላ የሚመጣ መሆኑን ሲያዩ ይደነቃሉ። #ዳን. 7፥7፤ ራዕ. 11፥7፤ መዝ. 69፥28።
9“ጥበብ ያለው አእምሮ የሚፈለገው እዚህ ላይ ነው፤ ሰባቱ ራሶች፥ ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ናቸው፤ 10እንዲሁም ሰባት ነገሥታት ናቸው፤ አምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱ አሁን አለ፤ ሌላው ገና አልመጣም፤ እርሱ ሲመጣ ለጥቂት ጊዜ ብቻ መቈየት አለበት። 11ስምንተኛው ንጉሥ ቀድሞ የነበረውና አሁን የሌለው አውሬ ነው፤ እርሱ ከሰባቱ አንዱ ነው፤ ወደ ጥፋትም ይሄዳል።
12“ያየሃቸው ዐሥሩ ቀንዶች ገና ያልነገሡ ዐሥር ነገሥታት ናቸው፤ ነገር ግን ለአንዲት ሰዓት ከአውሬው ጋር እንዲነግሡ የመንገሥ ሥልጣን ያገኛሉ። #ዳን. 7፥24። 13እነዚህ ዐሥር ነገሥታት አንድ ሐሳብ አላቸው፤ እነርሱ ኀይላቸውንና ሥልጣናቸውን ለአውሬው ያስረክባሉ፤ 14እነርሱ በበጉ ላይ ጦርነት ይከፍታሉ፤ ነገር ግን በጉ የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ ድል ይነሣቸዋል፤ ከእርሱ ጋር ያሉት የተጠሩ የተመረጡና የታመኑ ናቸው።”
15መልአኩም እንዲህ አለኝ፤ “አመንዝራይቱ ተቀምጣባቸው ያየሃቸው ውሃዎች፥ ሕዝቦችና፥ ሰዎች፥ ወገኖችና የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ናቸው፤ 16አውሬውና ያየሃቸው ዐሥር ቀንዶች አመንዝራይቱን ይጠላሉ፤ ወደ ጥፋት ያደርሱአታል፤ ራቁትዋን ያስቀሩአታል፤ ሥጋዋን ይበላሉ፤ በእሳትም ያቃጥሏታል፤ 17ዕቅዱን እንዲፈጽሙ ይህን ሐሳብ በልባቸው ያኖረ እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል እስኪፈጸም እነርሱ በአንድ ሐሳብ ይስማማሉ፤ የመንገሥ ሥልጣናቸውንም ለአውሬው ያስረክባሉ።
18“ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት።”
Currently Selected:
የዮሐንስ ራእይ 17: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997