ከዚህ በኋላ ሰባቱን መላእክት “ሂዱ! የእግዚአብሔርን ቊጣ የያዙትን ሰባቱን ጽዋዎች በምድር ላይ አፍስሱ!” የሚል ከፍ ያለ ድምፅ ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ሰማሁ። የመጀመሪያው መልአክ ሄደና ጽዋውን በምድር ላይ አፈሰሰ፤ የአውሬው ምልክት ባለባቸውና ለአውሬው ምስል በሚሰግዱ ሰዎች ላይ መጥፎና የሚያሠቃይ ቊስል ወጣባቸው። ሁለተኛው መልአክ ጽዋውን በባሕር ላይ አፈሰሰ፤ ባሕሩም እንደ ሞተ ሰው ደም ሆነ፤ በባሕሩ ይኖሩ የነበሩት ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ ሞቱ። ሦስተኛው መልአክ ጽዋውን በወንዞችና በውሃ ምንጮች ላይ አፈሰሰ፤ እነርሱም ደም ሆኑ፤ በውሃ ላይ ሥልጣን ያለው መልአክ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “ያለህና የነበርክ ቅዱስ ጌታ ሆይ! እንዲህ ስለ ፈረድክ አንተ ትክክለኛ ነህ፤ ሰዎች የቅዱሳንንና የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ ደም አጠጣሃቸው፤ ይህም የሚገባቸው ነው፤” በመሠዊያውም “አዎ! ሁሉን የምትችል ጌታ አምላክ ሆይ! ፍርዶችህ እውነትና ትክክል ናቸው” የሚል ድምፅ ሰማሁ። አራተኛው መልአክ ጽዋውን በፀሐይ ላይ አፈሰሰ፤ ፀሐይም ሰዎችን በግለትዋ ለማቃጠል ኀይል ተሰጣት፤ ሰዎች በታላቅ ግለት ተቃጠሉ፤ በእነዚህ መቅሠፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ፤ ንስሓ አልገቡም፤ እርሱንም አላከበሩም። አምስተኛው መልአክ ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ፤ የአውሬውም መንግሥት ጨለማ ሆነ፤ ሰዎች ከሥቃያቸው የተነሣ ምላሳቸውን ያኝኩ ነበር፤ ከሕመማቸውና ከቊስላቸው የተነሣ የሰማይን አምላክ ተራገሙ፤ ከሥራቸውም ንስሓ አልገቡም። ስድስተኛው መልአክ ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከምሥራቅ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ ለማዘጋጀት የወንዙ ውሃ ደረቀ። ከዘንዶው አፍና ከአውሬው አፍ፥ ከሐሰተኛውም ነቢይ አፍ ጓጉንቸሮች የሚመስሉ ሦስት ርኩሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ። እነርሱ ተአምራት የሚያደርጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸው፤ እነዚህ መናፍስት ሁሉን በሚችል አምላክ ታላቅ ቀን ለሚሆነው ጦርነት ሰዎችን ለመሰብሰብ ወደ ዓለም ነገሥታት ሁሉ ይሄዳሉ። “እነሆ! እኔ እንደ ሌባ በድንገት እመጣለሁ! ራቁቱን እንዳይሆንና ኀፍረቱን ሰዎች እንዳያዩበት ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ሰው የተመሰገነ ነው!” መናፍስቱም ነገሥታቱን በዕብራይስጥ አርማጌዶን በሚባል ስፍራ ሰበሰቡአቸው። ሰባተኛው መልአክ ጽዋውን በዐየር ላይ አፈሰሰ፤ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ካለው ዙፋን “ተፈጸመ!” የሚል ከፍተኛ ድምፅ ወጣ።
የዮሐንስ ራእይ 16 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ራእይ 16:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች