የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ራእይ 16:1-17

ራእይ 16:1-17 NASV

ከዚያም ለሰባቱ መላእክት፣ “ሂዱ፤ ሰባቱን የእግዚአብሔር ቍጣ ጽዋዎች በምድር ላይ አፍስሱ” የሚል ታላቅ ድምፅ ከቤተ መቅደሱ ሰማሁ። የመጀመሪያው መልአክ ሄዶ ጽዋውን በምድር ላይ አፈሰሰ፤ የአውሬውን ምልክት በተቀበሉትና ለምስሉም በሰገዱት ሰዎች ላይ ክፉኛ የሚያሠቃይ ቍስል ወጣባቸው። ሁለተኛው መልአክ ጽዋውን በባሕር ላይ አፈሰሰ፤ ባሕሩም እንደ ሞተ ሰው ደም ሆነ፤ በባሕሩ ውስጥ የሚኖሩ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ ሞቱ። ሦስተኛው መልአክ ጽዋውን በወንዞችና በውሃ ምንጮች ላይ አፈሰሰ፤ እነርሱም ደም ሆኑ። ከዚያም በውሆች ላይ ሥልጣን ያለው መልአክ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “ያለህና የነበርህ ቅዱሱ ሆይ፤ እንዲህ ስለ ፈረድህ፣ አንተ ጻድቅ ነህ፤ የቅዱሳንንና የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ፣ አንተም ደግሞ ደም እንዲጠጡ አደረግሃቸው፤ ይህ የሚገባቸው ነውና።” እንዲሁም ከመሠዊያው እንዲህ የሚል ድምፅ ሰማሁ፤ “አዎን፤ ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ ሆይ፤ ፍርድህ እውነትና ጽድቅ ነው።” አራተኛውም መልአክ ጽዋውን በፀሓይ ላይ አፈሰሰ፤ ፀሓይም ሰዎችን በእሳት እንድታቃጥል ኀይል ተሰጣት። እነርሱም በታላቅ ሐሩር ተቃጠሉ፤ በእነዚህም መቅሠፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ እንጂ ንስሓ አልገቡም፤ ክብርም አልሰጡትም። ዐምስተኛውም መልአክ ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ፤ የአውሬውም መንግሥት በጨለማ ተዋጠ፤ ሰዎችም ከሥቃያቸው የተነሣ ምላሳቸውን ያኝኩ ነበር፤ ደግሞም ከሥቃያቸውና ከቍስላቸው የተነሣ የሰማይን አምላክ ተሳደቡ እንጂ ከሥራቸው ንስሓ አልገቡም። ስድስተኛውም መልአክ ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከምሥራቅ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲዘጋጅላቸው የወንዙ ውሃ ደረቀ። ከዚያም ከዘንዶው አፍ፣ ከአውሬው አፍና ከሐሰተኛው ነቢይ አፍ እንቍራሪት የሚመስሉ ሦስት ርኩሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ። እነርሱም ምልክቶች የሚያደርጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸው፤ ሁሉን በሚችል አምላክ ታላቅ ቀን ለሚሆነው ጦርነት እንዲሰበስቧቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይሄዳሉ። “እነሆ፤ እንደ ሌባ እመጣለሁ፤ ዕራቍቱን እንዳይሆን ኀፍረቱም እንዳይታይ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ሰው ብፁዕ ነው።” እነርሱም ነገሥታቱን በዕብራይስጥ አርማጌዶን በሚባል ስፍራ ሰበሰቧቸው። ሰባተኛውም መልአክ ጽዋውን በአየር ላይ አፈሰሰ፤ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ካለው ዙፋንም “ተፈጸመ!” የሚል ታላቅ ድምፅ ወጣ።