የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ራእይ 14

14
በጉና መቶ አርባ አራቱ ሺህ ሰዎች
1ከዚህ በኋላ እነሆ በጉ በጽዮን ተራራ ላይ ቆሞ አየሁ፤ ከእርሱ ጋር የእርሱ ስምና የአባቱ ስም በግንባራቸው ላይ የተጻፈባቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ሰዎች ነበሩ። #ሕዝ. 9፥4፤ ራዕ. 7፥3። 2ከሰማይም የታላቅ ፏፏቴ ውሃ ድምፅና ታላቅ ነጐድጓድ የመሰለ ከፍተኛ ድምፅ ሰማሁ፤ የሰማሁትም ድምፅ በገና ደርዳሪዎች በገና እየደረደሩ የሚያሰሙትን ድምፅ ይመስል ነበር። 3በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች፥ በሽማግሌዎችም ፊት መቶ አርባ አራቱ ሺህ ሰዎች አዲስ መዝሙር ዘመሩ፤ ይህን መዝሙር ከምድር ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራቱ ሺህ ሰዎች በቀር ማንም ሊማረው አልቻለም። 4እነርሱ ድንግሎች ስለ ሆኑ ከሴቶች ጋር ግንኙነት በማድረግ አልረከሱም፤ በጉ ወደሚሄድበትም ሁሉ ይከተሉታል። እነርሱ ለእግዚአብሔርና ለበጉ ከሰዎች መካከል እንደ በኲራት የቀረቡ ናቸው። 5እነርሱ ሐሰት ተናግረው አያውቁም፤ ነቀፋም የሌለባቸው ናቸው።
የእግዚአብሔርን ፍርድ የሚያስታውቁ ሦስቱ መላእክት
6ከዚህ በኋላ በምድር ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ፥ ነገድ፥ ልዩ ልዩ ቋንቋዎችን ለሚናገሩና ለተለያዩ ወገኖች ሁሉ ለማብሠር ዘለዓለማዊውን ወንጌል የያዘ ሌላ መልአክ በሰማይ መካከል ሲበር አየሁ። 7በታላቅ ድምፅም “እግዚአብሔርን ፍሩ! አክብሩትም! የእርሱ የፍርድ ሰዓት ደርሶአል፤ ሰማይንና ምድርን ባሕርንና የውሃ ምንጮችን ለፈጠረ አምላክ ስገዱ!” አለ።
8ሌላም ሁለተኛው መልአክ “የሚያሰክረውን የዝሙትዋን ወይን ጠጅ ለሕዝቦች ሁሉ ያጠጣች ያቺ ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች!” እያለ የመጀመሪያውን መልአክ ተከተለ። #ኢሳ. 21፥9፤ ኤር. 51፥8፤ ራዕ. 18፥2።
9ሌላ ሦስተኛ መልአክም ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ እያለ ተከተላቸው፤ “ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግዱ፥ ምልክቱን በግንባራቸው ወይም በእጃቸው የሚያደርጉ ሁሉ፥ 10የእግዚአብሔርን የቊጣ የወይን ጠጅ ይጠጣሉ፤ ይህም የወይን ጠጅ ሳይበረዝ በቊጣው ጽዋ የተቀዳ ነው፤ እንዲሁም በቅዱሳን መላእክት ፊትና በበጉ ፊት በእሳትና በዲን ይሠቃያሉ፤ #ኢሳ. 51፥17፤ ዘፍ. 19፥24፤ ሕዝ. 38፥22። 11እነርሱን ከሚያሠቃየው እሳት የሚወጣው ጢስ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ወደ ላይ ይወጣል፤ ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግዱ የስሙንም ምልክት ያደረጉ ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም።” #ኢሳ. 34፥10።
12የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ከሚጠብቁና ኢየሱስንም በማመን ከሚጸኑ ቅዱሳን የሚጠበቀው ትዕግሥት እዚህ ላይ ነው።
13ከሰማይም እንዲህ የሚል ድምፅ ሰማሁ፤ ይህን ጻፍ፤ “ከእንግዲህ ወዲህ የጌታ ኢየሱስ ሆነው የሚሞቱ የተባረኩ ናቸው!” መንፈስ ቅዱስም “አዎ! ከድካማቸው እንዲያርፉ ሥራቸው ይከተላቸዋል” ይላል።
የጌታ ቊጣ በምድር ላይ
14ከዚህ በኋላ ተመለከትኩ፤ እነሆ፥ ነጭ ደመና አየሁ፤ በደመናው ላይ የሰውን ልጅ የሚመስል ተቀምጦአል፤ በራሱ ላይ የወርቅ አክሊል አድርጎአል፤ በእጁም ስለታም ማጭድ ይዞአል፤ #ዳን. 7፥13። 15ሌላ መልአክ ከመቅደሱ ወጣና በደመና ላይ የተቀመጠውን ከፍ ባለ ድምፅ “የምድር መከር ደርሶአል! የዐጨዳ ሰዓትም ቀርቦአል!” #ኢዩ. 3፥13። 16በደመናው ላይ የተቀመጠውም ማጭዱን ወደ ምድር ሰደደ፤ ምድርም ታጨደች።
17ሌላ መልአክም በሰማይ ካለው መቅደስ ወጣ፤ እርሱም ስለታም ማጭድ ይዞ ነበር።
18በእሳት ላይ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከመሠዊያው አጠገብ ወጣና ስለታም ማጭድ የያዘውን መልአክ “የዘለላዎቹ ፍሬዎች ስለ በሰሉ ስለታም ማጭድህን ስደድ! የወይን ዘለላዎችን ሁሉ ከምድር ወይን ቈርጠህ ሰብስብ!” በማለት ከፍ ባለ ድምፅ ጮኸ። 19መልአኩም ማጭዱን ወደ ምድር ሰደደው፤ የምድርንም ወይን ዘለላ ቈረጠ፤ በታላቁም የእግዚአብሔር ቊጣ መጭመቂያ ውስጥ ጣለው። 20ከከተማው ውጪ ባለው በወይን መጭመቂያም ተጨመቀ፤ ከመጭመቂያውም እስከ ፈረስ ልጓም ወደ ላይ ከፍ ያለና ሦስት መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት የሚደርስ ደም ወጥቶ ፈሰሰ። #ኢሳ. 63፥3፤ ሰቆ.ኤ. 1፥15፤ ራዕ. 19፥15።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ