መጽሐፈ መዝሙር 94
94
እግዚአብሔር የሁሉ ፈራጅ መሆኑ
1እግዚአብሔር ሆይ!
አንተ በቀልን የምትመልስ አምላክ ነህ፤
ስለዚህ ፍርድህን ግለጥ!
2አንተ የዓለም ፈራጅ ነህ፤
ስለዚህ ተነሥ፤
ለትዕቢተኞች የሚገባቸውን ቅጣት ስጣቸው።
3ክፉዎች የሚታበዩት እስከ መቼ ነው?
እግዚአብሔር ሆይ! ኧረ እስከ መቼ ነው?
4ክፉ አድራጊዎች ሁሉ በድንፋታና
በትዕቢታዊ ንግግሮች የተሞሉ ናቸው።
5እግዚአብሔር ሆይ! ሕዝብህን ያደቃሉ፤
የአንተን ወገኖች ይጨቊናሉ።
6ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶችና
አባትና እናት የሌላቸውን ልጆች ይገድላሉ፤
በምድራችን የሚኖሩትንም መጻተኞች ያጠፋሉ።
7ይህንንም ሁሉ እያደረጉ
“እግዚአብሔር አያየንም፤
የእስራኤል አምላክ አይመለከተንም” ይላሉ።
8ከሕዝብ መካከል እናንተ አላዋቂዎች ይህን አስተውሉ፤
እናንተ ሞኞች ሆይ! አስተዋዮች የምትሆኑት መቼ ነው?
9ጆሮን የፈጠረ አምላክ አይሰማምን?
ዐይንንስ የፈጠረ አምላክ አያይምን?
10ሕዝቦችን የሚገሥጸው አይቀጣምን
የሰውን ዘር የሚያስተምረው ዕውቀት የለውምን?
11እግዚአብሔር የሰዎችን ሁሉ ሐሳብና፥
ከንቱነታቸውን ያውቃል። #1ቆሮ. 3፥20።
12እግዚአብሔር ሆይ! አንተ የምትገሥጸውና
ሕግህንም የምታስተምረው ሰው እንዴት የተባረከ ነው!
13ለክፉዎች ጒድጓድ እስኪቈፈር ድረስ
እርሱን በመከራ ቀኖች ታሳርፈዋለህ።
14እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልም፤
የእርሱ የሆኑትንም አይተዋቸውም።
15ፍትሕ እንደገና የዳኝነት መሠረት ትሆናለች፤
ልበ ቅኖችም ሁሉ ይደግፉአታል።
16ዐመፀኞችን ለመቃወም ከጐኔ የሚቆም ማነው?
ከክፉ አድራጊዎችስ ጋር ስለ እኔ የሚከራከር ማን ነው?
17እግዚአብሔር ባይረዳኝ ኖሮ፥
ፈጥኜ ወደ ሙታን ዓለም በወረድኩ ነበር።
18“ለመውደቅ ተቃርቤአለሁ” ባልኩ ጊዜ
እግዚአብሔር ሆይ!
ዘለዓለማዊ ፍቅርህ ደግፎ አቆመኝ።
19አስጨናቂ ሐሳብ ልቤን በሞላው ጊዜ
ማጽናናትህ ደስታን ሰጠኝ።
20በሕግ ሽፋን በተቀነባበረ ተንኰል
ለተዛባ ፍትሕ ተባባሪ ትሆናለህን?
21እነርሱ በደጋግ ሰዎች ላይ ያሤራሉ፤
በንጹሓን ሰዎች ላይም የሞት ፍርድ ይበይናሉ።
22ለእኔ ግን እግዚአብሔር መከታዬ ነው፤
አምላኬ መጠጊያዬ ነው።
23እርሱ ስለ ክፋታቸው ይቀጣቸዋል፤
ስለ ኃጢአታቸውም ይደመስሳቸዋል፤
እግዚአብሔር አምላካችን ያጠፋቸዋል።
Currently Selected:
መጽሐፈ መዝሙር 94: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997