የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 69:16-36

መጽሐፈ መዝሙር 69:16-36 አማ05

እግዚአብሔር ሆይ! ቸርነት በተሞላበት ፍቅርህ ጸሎቴን ስማ፤ በታላቁ ምሕረትህ ወደ እኔ ተመለስ። ከእኔ ከአገልጋይህ ፊትህን አትሰወር፤ በከባድ ጭንቀት ላይ ስለ ሆንኩ ፈጥነህ ስማኝ። ወደ እኔ ቀርበህ ተቤዠኝ፤ ከጠላቶቼም አድነኝ። ምን ያኽል እንደምሰደብ አንተ ታውቃለህ፤ ምን ያኽል እንደ ተዋረድኩና ክብሬም እንደ ተቀነሰ ታስተውላለህ፤ እነሆ፥ ጠላቶቼ ሁሉ በፊትህ ናቸው። ስድብ ልቤን ስለ ሰበረው ተስፋ ቈረጥኩ፤ የሚያስተዛዝነኝ ሰው ፈለግኹ፤ ነገር ግን ማንም አልነበረም፤ የሚያጽናናኝ ሰው ፈለግኹ፤ ነገር ግን ማንም አልተገኘም። በምግቤ ውስጥ ሐሞት ቀላቀሉ፤ በጠማኝም ጊዜ ሆምጣጤ ሰጡኝ። በፊታቸው የተዘረጋው ማእድ ወጥመድና የሚመገቡትም ምግብ የመውደቂያቸውና የመጥፊያቸው ምክንያት ይሁን። ዐይናቸው እንዳያይ ይጨልም፤ ወገባቸው ሁልጊዜ ይንቀጥቀጥ። ኀይለኛ ቊጣህን በላያቸው አፍስስ፤ የቊጣህ መቅሠፍትም ይድረስባቸው። መኖሪያቸው ወና ይሁን፤ በቤታቸው ውስጥ አንድም ሰው አይኑር። አንተ የቀጣሃቸውን ሰዎች ያሳድዳሉ፤ አንተ ባቈሰልካቸው ሰዎች ላይ ሥቃይ ይጨምራሉ። በበደላቸው ላይ በደልን ጨምርባቸው፤ ይቅርታም አታድርግላቸው። ስሞቻቸው ከሕያዋን መዝገብ ይደምሰሱ፤ ከደጋግ ሰዎችም ጋር አይቈጠሩ። እኔ ግን በሥቃይና ተስፋ በመቊረጥ ላይ ስለምገኝ አምላክ ሆይ! ጠብቀኝ፤ አድነኝም። እግዚአብሔርን በመዝሙር አመሰግነዋለሁ፤ በምስጋናም መዝሙር ታላቅነቱን እገልጣለሁ። ይህም የተሟላ ዕድገት ያለው ኰርማ ወይም ወይፈን ከመሠዋት ይልቅ እግዚአብሔርን የበለጠ ያስደስተዋል። ትሑታን ይህን ባዩ ጊዜ ደስ ይላቸዋል፤ በጸሎት እግዚአብሔርን የምትሹ በርቱ። እግዚአብሔር የችግረኞችን ጩኸት ይሰማል፤ በእስር ቤት ያሉትን ወገኖቹንም ችላ አይላቸውም። ሰማይና ምድር፥ ባሕሮችና በውስጣቸው የሚኖሩ ተንቀሳቃሽ ፍጥረቶች ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግኑት። እርሱ ጽዮንን ያድናል፤ የይሁዳንም ከተሞች ያድሳል፤ ሕዝቡም በዚያ ይኖራሉ፤ ምድሪቱንም የራሳቸው ያደርጋሉ። የአገልጋዮቹም ዘሮች ይወርሱአታል፤ እርሱን የሚወዱ ሁሉ እዚያ ይኖራሉ።