መዝሙር 69:16-36
መዝሙር 69:16-36 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ በጎ ናትና ስማኝ፤ እንደ ርኅራኄም ብዛት መለስ በልልኝ። ፊትህን ከባሪያህ አትሰውር፤ ጭንቅ ውስጥ ነኝና ፈጥነህ መልስልኝ። ወደ እኔ ቀርበህ ታደገኝ፤ ስለ ጠላቶቼም ተቤዠኝ። የደረሰብኝን ስድብ፣ ዕፍረትና ውርደት ታውቃለህ፤ ጠላቶቼንም አንድ በአንድ ታውቃቸዋለህ። ስድብ ልቤን ጐድቶታል፤ ተስፋዬም ተሟጥጧል፤ አስተዛዛኝ ፈለግሁ፤ አላገኘሁምም፤ አጽናኝም ፈለግሁ፤ አንድም አልነበረም። ምግቤን ከሐሞት ቀላቀሉ፤ ለጥማቴም ሆምጣጤ ሰጡኝ። የቀረበላቸው ማእድ ወጥመድ ይሁንባቸው፤ ለማኅበራቸውም አሽክላ ይሁን። ዐይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ፤ ጀርባቸውም ዘወትር ይጕበጥ። መዓትህን በላያቸው አፍስስ፤ የቍጣህም መቅሠፍት ድንገት ይድረስባቸው። ሰፈራቸው ባድማ ይሁን፤ በድንኳኖቻቸው የሚኖር አይገኝ፤ አንተ የመታሃቸውን አሳድደዋልና፤ ያቈሰልሃቸውንም ሥቃያቸውን አባብሰዋል። በበደላቸው በደል ጨምርባቸው፤ ወደ ጽድቅህም አይግቡ። ከሕይወት መጽሐፍ ይደምሰሱ፤ ከጻድቃንም ጋር አይጻፉ። ነገር ግን እኔ በሥቃይና በጭንቅ ላይ እገኛለሁ፤ አምላክ ሆይ፤ ማዳንህ ደግፎ ይያዘኝ። የእግዚአብሔርን ስም በዝማሬ አወድሳለሁ፤ በምስጋናም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ። ከበሬ ይልቅ፣ ቀንድና ጥፍር ካበቀለ እንቦሳ ይልቅ ይህ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል። ድኾች ይህን ያያሉ፤ ደስም ይላቸዋል፤ እናንተ እግዚአብሔርን የምትሹ ልባችሁ ይለምልም! እግዚአብሔር ችግረኞችን ይሰማልና፤ በእስራት ያለውንም ሕዝቡን አይንቅም። ሰማይና ምድር፣ ባሕርም፣ በውስጣቸውም የሚንቀሳቀስ ሁሉ ያመስግኑት። እግዚአብሔር ጽዮንን ያድናታልና፤ የይሁዳንም ከተሞች መልሶ ይሠራቸዋልና፤ ሕዝቡም በዚያ ይሰፍራል፤ ይወርሳታልም። የባሪያዎቹም ዘሮች ይወርሷታል፤ ስሙንም የሚወድዱ በዚያ ይኖራሉ።
መዝሙር 69:16-36 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ! ቸርነት በተሞላበት ፍቅርህ ጸሎቴን ስማ፤ በታላቁ ምሕረትህ ወደ እኔ ተመለስ። ከእኔ ከአገልጋይህ ፊትህን አትሰወር፤ በከባድ ጭንቀት ላይ ስለ ሆንኩ ፈጥነህ ስማኝ። ወደ እኔ ቀርበህ ተቤዠኝ፤ ከጠላቶቼም አድነኝ። ምን ያኽል እንደምሰደብ አንተ ታውቃለህ፤ ምን ያኽል እንደ ተዋረድኩና ክብሬም እንደ ተቀነሰ ታስተውላለህ፤ እነሆ፥ ጠላቶቼ ሁሉ በፊትህ ናቸው። ስድብ ልቤን ስለ ሰበረው ተስፋ ቈረጥኩ፤ የሚያስተዛዝነኝ ሰው ፈለግኹ፤ ነገር ግን ማንም አልነበረም፤ የሚያጽናናኝ ሰው ፈለግኹ፤ ነገር ግን ማንም አልተገኘም። በምግቤ ውስጥ ሐሞት ቀላቀሉ፤ በጠማኝም ጊዜ ሆምጣጤ ሰጡኝ። በፊታቸው የተዘረጋው ማእድ ወጥመድና የሚመገቡትም ምግብ የመውደቂያቸውና የመጥፊያቸው ምክንያት ይሁን። ዐይናቸው እንዳያይ ይጨልም፤ ወገባቸው ሁልጊዜ ይንቀጥቀጥ። ኀይለኛ ቊጣህን በላያቸው አፍስስ፤ የቊጣህ መቅሠፍትም ይድረስባቸው። መኖሪያቸው ወና ይሁን፤ በቤታቸው ውስጥ አንድም ሰው አይኑር። አንተ የቀጣሃቸውን ሰዎች ያሳድዳሉ፤ አንተ ባቈሰልካቸው ሰዎች ላይ ሥቃይ ይጨምራሉ። በበደላቸው ላይ በደልን ጨምርባቸው፤ ይቅርታም አታድርግላቸው። ስሞቻቸው ከሕያዋን መዝገብ ይደምሰሱ፤ ከደጋግ ሰዎችም ጋር አይቈጠሩ። እኔ ግን በሥቃይና ተስፋ በመቊረጥ ላይ ስለምገኝ አምላክ ሆይ! ጠብቀኝ፤ አድነኝም። እግዚአብሔርን በመዝሙር አመሰግነዋለሁ፤ በምስጋናም መዝሙር ታላቅነቱን እገልጣለሁ። ይህም የተሟላ ዕድገት ያለው ኰርማ ወይም ወይፈን ከመሠዋት ይልቅ እግዚአብሔርን የበለጠ ያስደስተዋል። ትሑታን ይህን ባዩ ጊዜ ደስ ይላቸዋል፤ በጸሎት እግዚአብሔርን የምትሹ በርቱ። እግዚአብሔር የችግረኞችን ጩኸት ይሰማል፤ በእስር ቤት ያሉትን ወገኖቹንም ችላ አይላቸውም። ሰማይና ምድር፥ ባሕሮችና በውስጣቸው የሚኖሩ ተንቀሳቃሽ ፍጥረቶች ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግኑት። እርሱ ጽዮንን ያድናል፤ የይሁዳንም ከተሞች ያድሳል፤ ሕዝቡም በዚያ ይኖራሉ፤ ምድሪቱንም የራሳቸው ያደርጋሉ። የአገልጋዮቹም ዘሮች ይወርሱአታል፤ እርሱን የሚወዱ ሁሉ እዚያ ይኖራሉ።
መዝሙር 69:16-36 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የውኃው ማዕበል አያስጥመኝ፥ ጥልቁም አይዋጠኝ፥ ጉድጓድም አፉን በእኔ ላይ አይዝጋ። አቤቱ፥ ቸርነትህ መልካም ናትና ስማኝ። እንደ ርኅራኄህም ብዛት ወደ እኔ ተመልከት፥ ከባርያህም ፊትህን አትሰውር፥ ተጨንቄአለሁና ፈጥነህ መልስልኝ። ወደ ነፍሴ ቀርበህ ተቤዣት፥ ስለ ጠላቶቼም አድነኝ። አንተ ስድቤን እፍረቴንም ነውሬንም ታውቃለህ፥ የሚያስጨንቁኝ ሁሉ በፊትህ ናቸው። ስድብ እስክታመም ድረስ ልቤን ሰበረው፥ አስተዛዛኝም ተመኘሁ አላገኘሁም፥ የሚያጽናናኝም አጣሁ። ለመብሌ ሐሞት ሰጡኝ፥ ለጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ። ማዕዳቸው በፊታቸው ለወጥመድ ለፍዳ ለዕንቅፋት ትሁንባቸው፥ ዐይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ፥ ወገባቸውም ዘወትር ይንቀጥቀጥ። መዓትህን በላያቸው አፍስስ፥ የቁጣህ መቅሠፍትም ያግኛቸው። ማደሪያቸው በረሃ ትሁን፥ በድንኳኖቻቸውም የሚቀመጥ አይገኝ፥ አንተ የቀሠፍኸውን እነርሱ አሳድደዋልና፥ ባቈሰልከውም ላይ ጥዝጣዜ ጨመሩ። በበደል ላይ በደልን ጨምርባቸው፥ በጽድቅህም አይግቡ። ከሕያዋን መጽሐፍ ይደምሰሱ፥ ከጻድቃንም ጋር አይጻፉ። እኔ ችግረኛና ቁስለኛ ነኝ፥ አቤቱ፥ መድኃኒትህ ያቁመኝ። የእግዚአብሔርን ስም በዝማሬ አመሰግናለሁ፥ በምስጋናም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ። ቀንድና ሰኰና ካበቀለ ኰርማ ወይም ወይፈን ይልቅ ጌታን ደስ ያሰኘዋል። ችግረኞች ያያሉ ደስ ይላቸዋል፥ እግዚአብሔርን ፈልጉ ሕያዋንም ሁኑ። ጌታ ችግረኞችን ሰምቶአልና፥ እስረኞቹንም አልናቀምና። ሰማይና ምድር ባሕርም በእርሷም የሚንቀሳቀስ ሁሉ ያመሰግኑታል። እግዚአብሔር ጽዮንን ያድናታልና፥ የይሁዳንም ከተሞች ይሠራልና፥ በዚያም ይቀመጣሉ ይወርሱአትማል።