መጽሐፈ መዝሙር 44:9-26

መጽሐፈ መዝሙር 44:9-26 አማ05

አሁን ግን ጣልከን፤ አዋረድከንም፤ ከሚዘምተው ሠራዊታችን ጋር አብረህ መውጣትን ትተሃል። ከጠላቶቻችን ፊት እንድንሸሽ አደረግኸን፤ ጠላቶቻችንም ያለንን ሀብት ሁሉ ዘረፉን። እንደሚታረዱ በጎች አደረግኸን፤ በአሕዛብ ምድር በተንከን። ሕዝብህን በአነስተኛ ዋጋ ሸጥከው፤ እርሱንም በመሸጥ ምንም አላተረፍክም። በጐረቤቶቻችን የምንነቀፍ አደረግኸን፤ በዙሪያችን ላሉትም መዘባበቻና መሳለቂያ አደረግኸን። በሕዝቦች መካከል መተረቻ አደረግኸን፤ እነርሱም ራሳቸውን ይነቀንቁብናል። ውርደቴ ዘወትር በፊቴ ነው፤ ፊቴንም ኀፍረት ሸፍኖታል። እንዲህም የሆንኩት ጠላቶቼ በሚበቀሉኝ ጊዜ ሌሎች ሰዎች ሲያፌዙብኝና ሲሳለቁብኝ በመስማቴ ነው። ይህም ሁሉ የደረሰብን አንተን ሳንረሳና ቃል ኪዳንህንም ሳናፈርስ ነው። ልባችን ለአንተ እምነተቢስ አልሆነም፤ እግራችንም ከአንተ መንገድ አልወጣም። ነገር ግን አራዊት በሚኖሩበት ስፍራ ሰብረኸናል። በድቅድቅ ጨለማም ሸፍነኸናል። የአምላካችንን ስም ረስተን ቢሆን፥ ወደ ባዕዳን አማልክት እጆቻችንን ዘርግተን ቢሆን፥ አንተ የተሰወረውን ሐሳባችንን ስለምታውቅ በደላችንን ገልጠህ ባየህብን ነበር። ነገር ግን ስለ አንተ በየቀኑ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎችም ተቈጥረናል። ጌታ ሆይ! ንቃ! ስለምንስ ታንቀላፋለህ? ተነሥ! ለዘለዓለም አትተወን! መጨቈናችንንና ችግራችንን ቸል በማለት ስለምን ከእኛ ትሰወራለህ? መሬት እስክንነካ ድረስ አጐንብሰናል፤ በምድር ላይም ተዘርረናል። ተነሥ እኛን ለመርዳት ና! ስለ ዘለዓለማዊው ፍቅርህም ተቤዠን!