መዝሙር 44:9-26
መዝሙር 44:9-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አሁን ግን እነሆ ትተኸናል፤ አሳፍረኸናልም፤ ከሰራዊታችንም ጋራ አትወጣም። ከጠላት ፊት እንድናፈገፍግ አደረግኸን፤ ባላንጣዎቻችንም ዘረፉን። እንደሚታረዱ በጎች አደረግኸን፤ በሕዝቦችም መካከል በተንኸን። ሕዝብህን በርካሽ ዋጋ ሸጥኸው፤ ከሽያጩም ያገኘኸው ትርፍ የለም። ለጎረቤቶቻችን ስድብ፣ በዙሪያችን ላሉትም መሣቂያና መዘበቻ አደረግኸን። በሕዝቦች ዘንድ መተረቻ፣ በሰዎች መካከል በንቀት ራስ መነቅነቂያ አደረግኸን። ውርደቴ ቀኑን ሙሉ በፊቴ ነው፤ ፊቴም ዕፍረትን ተከናንቧል። ይህም ከሚዘልፍና ከሚያላግጥ ሰው ድምፅ የተነሣ፣ ከጠላትና ከተበቃይ ሁኔታ የተነሣ ነው። አንተን ሳንረሳ፣ ለኪዳንህም ታማኝነታችንን ሳናጓድል፣ ይህ ሁሉ ደረሰብን። ልባችን ወደ ኋላ አላለም፤ እግራችንም ከመንገድህ አልወጣም። አንተ ግን ተኵላዎች በሚውሉበት ቦታ ሰባብረህ ጣልኸን፤ በሞት ጥላም ሸፈንኸን። የአምላካችንን ስም ረስተን፣ እጃችንንም ወደ ባዕድ አምላክ ዘርግተን ቢሆን ኖሮ፣ እግዚአብሔር ይህን ማወቅ ይሳነዋልን? እርሱ ልብ የሰወረውን የሚረዳ ነውና። ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቈጥረናል። ጌታ ሆይ፤ ንቃ! ለምንስ ትተኛለህ? ተነሥ፤ ለዘላለምም አትጣለን። ፊትህን ለምን ትሰውራለህ? መከራችንንና መጠቃታችንን ለምን ትረሳለህ? ነፍሳችን ዐፈር ውስጥ ሰጥማለች፤ ሆዳችንም ከምድር ጋራ ተጣብቋል። ተነሥና እርዳን! ስለ ምሕረትህ ስትል ተቤዠን።
መዝሙር 44:9-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አሁን ግን ጣልከን፤ አዋረድከንም፤ ከሚዘምተው ሠራዊታችን ጋር አብረህ መውጣትን ትተሃል። ከጠላቶቻችን ፊት እንድንሸሽ አደረግኸን፤ ጠላቶቻችንም ያለንን ሀብት ሁሉ ዘረፉን። እንደሚታረዱ በጎች አደረግኸን፤ በአሕዛብ ምድር በተንከን። ሕዝብህን በአነስተኛ ዋጋ ሸጥከው፤ እርሱንም በመሸጥ ምንም አላተረፍክም። በጐረቤቶቻችን የምንነቀፍ አደረግኸን፤ በዙሪያችን ላሉትም መዘባበቻና መሳለቂያ አደረግኸን። በሕዝቦች መካከል መተረቻ አደረግኸን፤ እነርሱም ራሳቸውን ይነቀንቁብናል። ውርደቴ ዘወትር በፊቴ ነው፤ ፊቴንም ኀፍረት ሸፍኖታል። እንዲህም የሆንኩት ጠላቶቼ በሚበቀሉኝ ጊዜ ሌሎች ሰዎች ሲያፌዙብኝና ሲሳለቁብኝ በመስማቴ ነው። ይህም ሁሉ የደረሰብን አንተን ሳንረሳና ቃል ኪዳንህንም ሳናፈርስ ነው። ልባችን ለአንተ እምነተቢስ አልሆነም፤ እግራችንም ከአንተ መንገድ አልወጣም። ነገር ግን አራዊት በሚኖሩበት ስፍራ ሰብረኸናል። በድቅድቅ ጨለማም ሸፍነኸናል። የአምላካችንን ስም ረስተን ቢሆን፥ ወደ ባዕዳን አማልክት እጆቻችንን ዘርግተን ቢሆን፥ አንተ የተሰወረውን ሐሳባችንን ስለምታውቅ በደላችንን ገልጠህ ባየህብን ነበር። ነገር ግን ስለ አንተ በየቀኑ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎችም ተቈጥረናል። ጌታ ሆይ! ንቃ! ስለምንስ ታንቀላፋለህ? ተነሥ! ለዘለዓለም አትተወን! መጨቈናችንንና ችግራችንን ቸል በማለት ስለምን ከእኛ ትሰወራለህ? መሬት እስክንነካ ድረስ አጐንብሰናል፤ በምድር ላይም ተዘርረናል። ተነሥ እኛን ለመርዳት ና! ስለ ዘለዓለማዊው ፍቅርህም ተቤዠን!
መዝሙር 44:9-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሁልጊዜ በእግዚአብሔር እንከብራለን፥ ስምህንም ለዘለዓለም እናመሰግናለን። አሁን ግን ጣልከን አሳፈርኸንም፥ ከሠራዊታችንም ጋር አትወጣም። ከጠላቶቻችንም ፊት ወደ ኋላችን መለስኸን፥ የሚጠሉንም ተነጣጠቁን። እንደ በጎች ሊበሉን ሰጠኸን፥ ወደ አሕዛብም በተንኸን። ሕዝብህን ያለ ዋጋ ሰጠህ፥ በመለወጣቸውም ትርፍ የለም። ለጎረቤቶቻችን ስድብ፥ በዙሪያችንም ላሉ መሣቂያና መዘበቻ አደረግኸን። በአሕዛብ ዘንድ ምሳሌ፥ በሕዝብም ዘንድ መናቂያ አደረግኸን። ጉስቁልናዬ ሁልጊዜ በፊቴ ነው፥ የፊቴም እፍረት ሸፈነኝ። ከሚሳደብና ከሚላገድ ቃል የተነሣ፥ ከጠላትና ከቂመኛ ፊት የተነሣ ነው። ይህ ሁሉ በእኛ ላይ ደረሰ፥ አልረሳንህም፥ ኪዳንህንም አልወነጀልንም። ልባችን ወደ ኋላው አልተመለሰም፥ ፍለጋችንም ከመንገድህ ፈቀቅ አላለም፥ በክፉ ስፍራ አዋርደኸናልና፥ በሞት ጥላም ሰውረኸናልና። የአምላካችንን ስም ረስተንስ ቢሆን፥ እጃችንንም ወደ ሌላ አምላክ አንሥተንስ ቢሆን፥ እግዚአብሔር ይህንን አይመረምርም ነበርን? እርሱ ልብ የሰወረውን ያውቃልና። ስለ አንተ ሁልጊዜ ተገድለናል፥ እንደሚታረዱም በጎች ሆነናል። አቤቱ፥ ንቃ፥ ለምንስ ትተኛለህ? ተነሥ፥ ለዘወትርም አትጣለን። ለምንስ ፊትህን ትሰውራለህ? መከራችንንና ጭንቃችንን ለምን ትረሳለህ? ነፍሳችን በመሬት ላይ ተጐሳቁላለችና፥ ሆዳችንም ከምድር ጋር ተጣብቃለችና።