መዝሙረ ዳዊት 44:9-26

መዝሙረ ዳዊት 44:9-26 መቅካእኤ

ሁልጊዜ በእግዚአብሔር እንከብራለን፥ ስምህንም ለዘለዓለም እናመሰግናለን። አሁን ግን ጣልከን አሳፈርኸንም፥ ከሠራዊታችንም ጋር አትወጣም። ከጠላቶቻችንም ፊት ወደ ኋላችን መለስኸን፥ የሚጠሉንም ተነጣጠቁን። እንደ በጎች ሊበሉን ሰጠኸን፥ ወደ አሕዛብም በተንኸን። ሕዝብህን ያለ ዋጋ ሰጠህ፥ በመለወጣቸውም ትርፍ የለም። ለጎረቤቶቻችን ስድብ፥ በዙሪያችንም ላሉ መሣቂያና መዘበቻ አደረግኸን። በአሕዛብ ዘንድ ምሳሌ፥ በሕዝብም ዘንድ መናቂያ አደረግኸን። ጉስቁልናዬ ሁልጊዜ በፊቴ ነው፥ የፊቴም እፍረት ሸፈነኝ። ከሚሳደብና ከሚላገድ ቃል የተነሣ፥ ከጠላትና ከቂመኛ ፊት የተነሣ ነው። ይህ ሁሉ በእኛ ላይ ደረሰ፥ አልረሳንህም፥ ኪዳንህንም አልወነጀልንም። ልባችን ወደ ኋላው አልተመለሰም፥ ፍለጋችንም ከመንገድህ ፈቀቅ አላለም፥ በክፉ ስፍራ አዋርደኸናልና፥ በሞት ጥላም ሰውረኸናልና። የአምላካችንን ስም ረስተንስ ቢሆን፥ እጃችንንም ወደ ሌላ አምላክ አንሥተንስ ቢሆን፥ እግዚአብሔር ይህንን አይመረምርም ነበርን? እርሱ ልብ የሰወረውን ያውቃልና። ስለ አንተ ሁልጊዜ ተገድለናል፥ እንደሚታረዱም በጎች ሆነናል። አቤቱ፥ ንቃ፥ ለምንስ ትተኛለህ? ተነሥ፥ ለዘወትርም አትጣለን። ለምንስ ፊትህን ትሰውራለህ? መከራችንንና ጭንቃችንን ለምን ትረሳለህ? ነፍሳችን በመሬት ላይ ተጐሳቁላለችና፥ ሆዳችንም ከምድር ጋር ተጣብቃለችና።