አምላኬ! አምላኬ! ለምን ተውከኝ? እኔን ከማዳን የራቅኸው ለምንድን ነው? ከመቃተት ድምፄስ የራቅኸው ለምንድን ነው? አምላኬ ሆይ! በቀን ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ አንተ ግን አትሰማኝም፤ በሌሊት እጣራለሁ፤ ዕረፍትም የለኝም። ሆኖም አንተ በእስራኤል የተመሰገንክ፥ በዙፋንህ ላይ ተቀምጠህ የምትገዛ ቅዱስ አምላክ ነህ። የቀድሞ አባቶቻችን በአንተ ተማመኑ፤ በአንተም ስለ ተማመኑ አዳንካቸው። ለእርዳታ ወደ አንተ በጮኹ ጊዜ አዳንካቸው፤ አንተን በተማመኑ ጊዜ አላሳፈርካቸውም። እኔ ግን ከሰው ሁሉ ያነስኩ ትል ነኝ፤ ሰዎች ያፌዙብኛል በሕዝብም ዘንድ የተናቅሁ ነኝ። የሚያዩኝ ሰዎች ሁሉ ይዘባበቱብኛል፤ ፊታቸውን ያኰሳትሩብኛል፤ ራሳቸውንም ይነቀንቁብኛል። “እግዚአብሔር ያድነው ዘንድ በእርሱ ተማምኖአልና የሚወደው ከሆነ እስቲ ያድነው” ይላሉ። በደኅና እንድወለድ ያደረግኸኝ አንተ ነህ፤ የእናቴን ጡት በምጠባበት በሕፃንነቴ ወራት እንኳ የጠበቅኸኝ አንተ ነህ። ከተወለድኩበት ቀን ጀምሮ በአንተ ጥበቃ ሥር ነኝ፤ ከልደቴ ጊዜም ጀምሮ አንተ አምላኬ ነህ። መከራ ሊደርስብኝ ስለ ተቃረበና የሚረዳኝም ስለሌለ እባክህ ከእኔ አትራቅ! ብዙ ጠላቶች እንደሚዋጉ በሬዎች ከበውኛል፤ እንደ ባሳን ተዋጊ ኰርማዎችም በዙሪያዬ ናቸው፤ የሚበላውን ነገር አድኖ ለመቦጫጨቅ እንደሚያገሣ አንበሳ ጠላቶቼ አፋቸውን ከፈቱብኝ። ጒልበቴ ደክሞ እንደ ውሃ ፈሰሰ፤ አጥንቶቼ ሁሉ ከመገጣጠሚያቸው ተለያዩ፤ ልቤም እንደ ሰም በውስጤ ቀለጠ። ጒሮሮዬ እንደ ሸክላ ደረቀ፤ ምላሴም ከላንቃዬ ጋር ተጣበቀ፤ እንደ ሞተ ሰው በትቢያ ላይ ተውከኝ። ክፉ ሰዎች እንደ ውሻ ስብስብ ከበቡኝ፤ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩ። አጥንቶቼ ተቈጠሩ፤ ጠላቶቼም አተኲረው እያዩ በማፌዝ ተመለከቱኝ። ልብሶቼን ተከፋፈሉ፤ በቀሚሴም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ። እግዚአብሔር ሆይ! ከእኔ አትራቅ፤ ረዳቴ ሆይ! እኔን ለመርዳት ፈጥነህ ድረስ። ነፍሴን ከሰይፍና ከእነዚያ ውሾች ኀይል አድነኝ። ከአንበሳ አፍ አድነኝ ከተዋጊ ጐሽ ቀንድም ጠብቀኝ።
መጽሐፈ መዝሙር 22 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መዝሙር 22:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች