መዝሙር 22:1-21

መዝሙር 22:1-21 NASV

አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውኸኝ? እኔን ከማዳን፣ ከመቃተቴም ቃል ለምን ራቅህ? አምላኬ ሆይ፤ በቀን ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ አንተ ግን አልመለስህልኝም፤ በሌሊት እንኳ አላረፍሁም። አንተ ግን ቅዱሱ ነጋሢ፤ የእስራኤልም ምስጋና ነህ። አባቶቻችን በአንተ ታመኑ፤ ተማመኑብህ፤ አንተም ታደግሃቸው። ወደ አንተ ጮኹ፤ ዳኑም፤ በአንተም ታመኑ፤ አላፈሩም። እኔ ግን ትል እንጂ ሰው አይደለሁም፤ ሰው ያላገጠብኝ፣ ሕዝብም የናቀኝ ነኝ። የሚያዩኝ ሁሉ ይሣለቁብኛል፤ ራሳቸውንም እየነቀነቁ እንዲህ እያሉ ይዘልፉኛል፤ “በእግዚአብሔር ተማምኗል፤ እንግዲህ እርሱ ያድነው፤ ደስ የተሠኘበትን፣ እስኪ ይታደገው።” አንተ ግን ከማሕፀን አወጣኸኝ፤ በእናቴም ጡት ሳለሁ፣ መታመኛ ሆንኸኝ። ከማሕፀን ስወጣም በአንተ ላይ ተጣልሁ፤ ከእናቴ ሆድ ጀምሮም አንተ አምላኬ ነህ። መከራ እየተቃረበ ነውና፣ የሚረዳኝም የለምና፣ ከእኔ አትራቅ። ብዙ ኰርማዎች ከበቡኝ፤ ኀይለኛ የባሳን በሬዎችም ዙሪያዬን ቆሙ። እንደሚነጥቅና እንደሚያገሣ አንበሳ፣ አፋቸውን ከፈቱብኝ። እንደ ውሃ ፈሰስሁ፤ ዐጥንቶቼም ሁሉ ከመጋጠሚያቸው ወለቁ፤ ልቤ እንደ ሰም ሆነ፤ በውስጤም ቀለጠ። ጕልበቴ እንደ ገል ደረቀ፤ ምላሴ ከላንቃዬ ጋራ ተጣበቀ፤ ወደ ሞት ዐፈርም አወረድኸኝ። ውሾች ከበቡኝ፤ የክፉዎች ሸንጎ በዙሪያዬ ተሰልፏል፤ እጆቼንና እግሮቼንም ቸነከሩኝ። ዐጥንቶቼን ሁሉ አንድ በአንድ መቍጠር እችላለሁ፤ እነርሱም አፍጥጠው ይመለከቱኛል። ልብሶቼን ተከፋፈሉ፤ በእጀ ጠባቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ። አንተ ግን፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከእኔ አትራቅ፤ ዐጋዤ ሆይ፤ እኔን ለመርዳት ፍጠን። ነፍሴን ከሰይፍ ታደጋት፤ ውድ ሕይወቴንም ከውሾች ጡጫ አድናት። ከአንበሶች አፍ አድነኝ፤ ከአውራሪስ ቀንድም ታደገኝ።