የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 119:49-64

መጽሐፈ መዝሙር 119:49-64 አማ05

ተስፋ የማደርገው በእርሱ ላይ ስለ ሆነ ለእኔ ለአገልጋይህ የሰጠኸውን የተስፋ ቃል አስብ። የተስፋ ቃልህ ሕይወቴን ስላደሰልኝ፥ በመከራዬ ጊዜ እንኳ እጽናናለሁ። ትዕቢተኞች ዘወትር ያፌዙብኛል፤ እኔ ግን ከትእዛዞችህ አልርቅም። እግዚአብሔር ሆይ! መጽናናትን የሚሰጠኝ ስለ ሆነ ከጥንት ጀምሮ የነበረውን ሕግህን አስታውሳለሁ። ክፉ ሰዎች ሕግህን ሲተላለፉ በማየቴ በብርቱ ተቈጣሁ። በምኖርበት ቦታ ሁሉ ሕጎችህ የመዝሙሬ አዝማቾች ናቸው። እግዚአብሔር ሆይ! በሌሊት ስምህን አስታውሳለሁ፤ በሕግህም ጸንቼ እኖራለሁ። ትእዛዞችህን ዘወትር ስለማከብር፥ በረከትን አገኘሁ። እግዚአብሔር ሆይ! እኔ የምፈልገው አንተን ብቻ ነው፤ ሕግህንም ለመጠበቅ ቃል እገባለሁ። በተስፋ ቃልህ መሠረት ምሕረት እንድታደርግልኝ ከልብ እለምንሃለሁ። አካሄዴን መርምሬ የተረዳሁት ስለ ሆነ ሥርዓትህን ለመከተል ቃል እገባለሁ። ያለ ማመንታት ትእዛዞችህን ለመፈጸም እተጋለሁ። ክፉዎች ወጥመድ ቢዘረጉብኝም እኔ ግን ሕግህን አልረሳም። ስለ ትክክለኛ ፍርድህ አንተን ለማመስገን በእኩለ ሌሊት እነሣለሁ። አንተን የሚፈሩትንና ሕግህን የሚያከብሩትን ሁሉ እወዳቸዋለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! ምድር በዘለዓለማዊው ፍቅርህ የተሞላች ናት፤ ሕጎችህን አስተምረኝ።