እግዚአብሔር ሆይ! የሕግህን ትርጒም አስተምረኝ፤ እኔም ዘወትር እከተለዋለሁ። ሕግህን ግለጥልኝ፤ እኔም አከብረዋለሁ፤ በሙሉ ልቤም እጠብቀዋለሁ። ትእዛዞችህ ስለሚያስደስቱኝ እንድፈጽማቸው እርዳኝ። ሀብት ለማግኘት ከመስገብገብ ይልቅ ሕግህን የመፈጸም ፍላጎት እንዲኖረኝ አድርግ። ወደ ከንቱ ነገር ከማዘንበል ጠብቀኝ፤ በቃልህ መሠረት ሕይወቴን አድስልኝ። ለእኔ ለአገልጋይህና ለሚፈሩህ ሁሉ የሰጠኸውን የተስፋ ቃል ፈጽም። ፍርድህ ትክክል ስለ ሆነ ከምፈራው ውርደት ጠብቀኝ። ትእዛዞችህን መጠበቅ እመኛለሁ፤ አንተ እውነተኛ ስለ ሆንክ ሕይወቴን አድስልኝ። እግዚአብሔር ሆይ! ዘለዓለማዊ ፍቅርህ ወደ እኔ ይድረስ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት አድነኝ። በቃልህ ስለምተማመን ለሚሰድቡኝ ሁሉ መልስ መስጠት እችላለሁ። ተስፋ የማደርገው የአንተን ፍርድ ስለ ሆነ ዘወትር እውነት እንድናገር እርዳኝ። ሕግህን ባለማቋረጥ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም እፈጽማለሁ። ትእዛዝህን መፈጸም ስለምወድ በፍጹም ነጻነት እኖራለሁ። ትእዛዞችህን በነገሥታት ፊት እናገራለሁ፤ ከቶም አላፍርም። በትእዛዞችህ የምደሰተው እነርሱን ስለምወዳቸው ነው። የምወዳቸውን ትእዛዞችህን አከብራለሁ፤ ስለ ሥርዓትህም በተመስጦ አሰላስላለሁ።
መጽሐፈ መዝሙር 119 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መዝሙር 119:33-48
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos