መጽሐፈ መዝሙር 119:25-48

መጽሐፈ መዝሙር 119:25-48 አማ05

ተሸንፌ ትቢያ ላይ ወድቄአለሁ፤ በሰጠኸኝ የተስፋ ቃል መሠረት ሕይወቴን አድስልኝ። አድራጎቴን ሁሉ ተናዘዝኩ፤ አንተም ሰማኸኝ፤ እንግዲህ ሕግህን አስተምረኝ። ሕግህን እንዳስተውል እርዳኝ፤ እኔም ድንቅ ሥራህን አሰላስላለሁ። ሐዘን በርትቶብኛል፤ በሰጠኸኝ የተስፋ ቃል መሠረት ኀይሌን አድስልኝ። ሐሰትን ከእኔ አርቅልኝ፤ በቸርነትህም ሕግህን አስተምረኝ። ታማኝ ለመሆንና ሕግህን ለመጠበቅ ወስኜአለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! በሕግህ ጸንቼአለሁ፤ እባክህ አታሳፍረኝ። ብዙ ማስተዋልን ስለ ሰጠኸኝ፤ ትእዛዞችህን በትጋት እፈጽማለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! የሕግህን ትርጒም አስተምረኝ፤ እኔም ዘወትር እከተለዋለሁ። ሕግህን ግለጥልኝ፤ እኔም አከብረዋለሁ፤ በሙሉ ልቤም እጠብቀዋለሁ። ትእዛዞችህ ስለሚያስደስቱኝ እንድፈጽማቸው እርዳኝ። ሀብት ለማግኘት ከመስገብገብ ይልቅ ሕግህን የመፈጸም ፍላጎት እንዲኖረኝ አድርግ። ወደ ከንቱ ነገር ከማዘንበል ጠብቀኝ፤ በቃልህ መሠረት ሕይወቴን አድስልኝ። ለእኔ ለአገልጋይህና ለሚፈሩህ ሁሉ የሰጠኸውን የተስፋ ቃል ፈጽም። ፍርድህ ትክክል ስለ ሆነ ከምፈራው ውርደት ጠብቀኝ። ትእዛዞችህን መጠበቅ እመኛለሁ፤ አንተ እውነተኛ ስለ ሆንክ ሕይወቴን አድስልኝ። እግዚአብሔር ሆይ! ዘለዓለማዊ ፍቅርህ ወደ እኔ ይድረስ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት አድነኝ። በቃልህ ስለምተማመን ለሚሰድቡኝ ሁሉ መልስ መስጠት እችላለሁ። ተስፋ የማደርገው የአንተን ፍርድ ስለ ሆነ ዘወትር እውነት እንድናገር እርዳኝ። ሕግህን ባለማቋረጥ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም እፈጽማለሁ። ትእዛዝህን መፈጸም ስለምወድ በፍጹም ነጻነት እኖራለሁ። ትእዛዞችህን በነገሥታት ፊት እናገራለሁ፤ ከቶም አላፍርም። በትእዛዞችህ የምደሰተው እነርሱን ስለምወዳቸው ነው። የምወዳቸውን ትእዛዞችህን አከብራለሁ፤ ስለ ሥርዓትህም በተመስጦ አሰላስላለሁ።