በአካሄዳቸው ነቀፋ የሌለባቸው፥ በእግዚአብሔር ሕግ መሠረት የሚኖሩ ሰዎች የተባረኩ ናቸው። ትእዛዞቹን የሚጠብቁ፥ በሙሉ ልባቸውም የሚፈልጉት፥ የተባረኩ ናቸው። የማይሳሳቱና በእግዚአብሔር መንገድ የሚሄዱ የተባረኩ ናቸው። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ሕጎችህን ሰጥተኸናል፤ በታማኝነት እንድንታዘዛቸውም ነግረኸናል፤ ድንጋጌህን በመጠበቅ ታማኝ ለመሆን በብርቱ እመኛለሁ። ትእዛዞችህን ሁሉ በጥንቃቄ ከአስተዋልኩ ኀፍረት ከቶ አይደርስብኝም። የሕግህን ፍጹምነት ባወቅሁ መጠን በንጹሕ ልብ አመሰግንሃለሁ። ሕግህን ስለምፈጽም ፈጽሞ አትተወኝ። ወጣቶች ሕይወታቸውን በንጽሕና መጠበቅ የሚችሉት ትእዛዞችህን በመፈጸም ነው። አንተን በሙሉ ልቤ ስለምፈልግህ ትእዛዞችህን እንዳላፈርስ ጠብቀኝ። አንተን እንዳልበድል ቃልህን በልቤ አኖራለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! አመሰግንሃለሁ፤ የአንተን ሕግ አስተምረኝ። አንተ የሰጠኸውን ሕግ ሁሉ መላልሼ አነባለሁ። የአንተን ትእዛዝ መፈጸም ብዙ ሀብት የማግኘትን ያኽል ያስደስተኛል። ሥርዓትህን አጠናለሁ፤ በምትመራኝ መንገድ ላይም አተኲራለሁ። በሕግህ ደስ ይለኛል፤ ቃልህንም አልረሳም። በሕይወት እንድኖርና የቃልህን ትምህርት እንድጠብቅ ለእኔ ለአገልጋይህ መልካም ነገር አድርግልኝ። በሕግህ ውስጥ ያለውን አስደናቂ እውነት ማየት እንድችል ዐይኖቼን ክፈትልኝ። እኔ በምድር ላይ በእንግድነት የምኖረው ለጥቂት ጊዜ ነው፤ ስለዚህ ትእዛዞችህን አትሰውርብኝ። ነፍሴ ሥርዓትህን ለማግኘት ሁልጊዜ በመናፈቅ ተጨነቀች። የተረገሙትንና ከትእዛዞችህ የሚያፈነግጡትን ትዕቢተኞች ትገሥጻለህ። እኔ ሕግህን ስለ ጠበቅሁ ስድባቸውንና ንቀታቸውን ከእኔ አርቅልኝ። መሪዎች ተሰብስበው በእኔ ላይ ቢዶልቱም እንኳ እኔ አገልጋይህ ግን ሕግህን አሰላስላለሁ። ትእዛዞችህ ያስደስቱኛል፤ መካሪዎቼም እነርሱ ናቸው። ተሸንፌ ትቢያ ላይ ወድቄአለሁ፤ በሰጠኸኝ የተስፋ ቃል መሠረት ሕይወቴን አድስልኝ። አድራጎቴን ሁሉ ተናዘዝኩ፤ አንተም ሰማኸኝ፤ እንግዲህ ሕግህን አስተምረኝ። ሕግህን እንዳስተውል እርዳኝ፤ እኔም ድንቅ ሥራህን አሰላስላለሁ። ሐዘን በርትቶብኛል፤ በሰጠኸኝ የተስፋ ቃል መሠረት ኀይሌን አድስልኝ። ሐሰትን ከእኔ አርቅልኝ፤ በቸርነትህም ሕግህን አስተምረኝ። ታማኝ ለመሆንና ሕግህን ለመጠበቅ ወስኜአለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! በሕግህ ጸንቼአለሁ፤ እባክህ አታሳፍረኝ። ብዙ ማስተዋልን ስለ ሰጠኸኝ፤ ትእዛዞችህን በትጋት እፈጽማለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! የሕግህን ትርጒም አስተምረኝ፤ እኔም ዘወትር እከተለዋለሁ። ሕግህን ግለጥልኝ፤ እኔም አከብረዋለሁ፤ በሙሉ ልቤም እጠብቀዋለሁ። ትእዛዞችህ ስለሚያስደስቱኝ እንድፈጽማቸው እርዳኝ። ሀብት ለማግኘት ከመስገብገብ ይልቅ ሕግህን የመፈጸም ፍላጎት እንዲኖረኝ አድርግ። ወደ ከንቱ ነገር ከማዘንበል ጠብቀኝ፤ በቃልህ መሠረት ሕይወቴን አድስልኝ። ለእኔ ለአገልጋይህና ለሚፈሩህ ሁሉ የሰጠኸውን የተስፋ ቃል ፈጽም። ፍርድህ ትክክል ስለ ሆነ ከምፈራው ውርደት ጠብቀኝ። ትእዛዞችህን መጠበቅ እመኛለሁ፤ አንተ እውነተኛ ስለ ሆንክ ሕይወቴን አድስልኝ። እግዚአብሔር ሆይ! ዘለዓለማዊ ፍቅርህ ወደ እኔ ይድረስ፤ በተስፋ ቃልህም መሠረት አድነኝ። በቃልህ ስለምተማመን ለሚሰድቡኝ ሁሉ መልስ መስጠት እችላለሁ። ተስፋ የማደርገው የአንተን ፍርድ ስለ ሆነ ዘወትር እውነት እንድናገር እርዳኝ። ሕግህን ባለማቋረጥ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም እፈጽማለሁ። ትእዛዝህን መፈጸም ስለምወድ በፍጹም ነጻነት እኖራለሁ። ትእዛዞችህን በነገሥታት ፊት እናገራለሁ፤ ከቶም አላፍርም። በትእዛዞችህ የምደሰተው እነርሱን ስለምወዳቸው ነው። የምወዳቸውን ትእዛዞችህን አከብራለሁ፤ ስለ ሥርዓትህም በተመስጦ አሰላስላለሁ። ተስፋ የማደርገው በእርሱ ላይ ስለ ሆነ ለእኔ ለአገልጋይህ የሰጠኸውን የተስፋ ቃል አስብ። የተስፋ ቃልህ ሕይወቴን ስላደሰልኝ፥ በመከራዬ ጊዜ እንኳ እጽናናለሁ። ትዕቢተኞች ዘወትር ያፌዙብኛል፤ እኔ ግን ከትእዛዞችህ አልርቅም። እግዚአብሔር ሆይ! መጽናናትን የሚሰጠኝ ስለ ሆነ ከጥንት ጀምሮ የነበረውን ሕግህን አስታውሳለሁ። ክፉ ሰዎች ሕግህን ሲተላለፉ በማየቴ በብርቱ ተቈጣሁ። በምኖርበት ቦታ ሁሉ ሕጎችህ የመዝሙሬ አዝማቾች ናቸው። እግዚአብሔር ሆይ! በሌሊት ስምህን አስታውሳለሁ፤ በሕግህም ጸንቼ እኖራለሁ። ትእዛዞችህን ዘወትር ስለማከብር፥ በረከትን አገኘሁ። እግዚአብሔር ሆይ! እኔ የምፈልገው አንተን ብቻ ነው፤ ሕግህንም ለመጠበቅ ቃል እገባለሁ። በተስፋ ቃልህ መሠረት ምሕረት እንድታደርግልኝ ከልብ እለምንሃለሁ። አካሄዴን መርምሬ የተረዳሁት ስለ ሆነ ሥርዓትህን ለመከተል ቃል እገባለሁ። ያለ ማመንታት ትእዛዞችህን ለመፈጸም እተጋለሁ። ክፉዎች ወጥመድ ቢዘረጉብኝም እኔ ግን ሕግህን አልረሳም። ስለ ትክክለኛ ፍርድህ አንተን ለማመስገን በእኩለ ሌሊት እነሣለሁ። አንተን የሚፈሩትንና ሕግህን የሚያከብሩትን ሁሉ እወዳቸዋለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! ምድር በዘለዓለማዊው ፍቅርህ የተሞላች ናት፤ ሕጎችህን አስተምረኝ። እግዚአብሔር ሆይ! የተስፋ ቃልህን ጠብቀሃል፤ ለእኔም ለአገልጋይህ ቸር ሆነሃል። በትእዛዞችህ ስለምተማመን አስተዋይነትንና ዕውቀትን ስጠኝ። አንተ እኔን ከመቅጣትህ በፊት እሳሳት ነበር፤ አሁን ግን ለቃልህ እታዘዛለሁ። አንተ ቸር ስለ ሆንክ ቸር የሆነውን ታደርጋለህ፤ ሕጎችህን አስተምረኝ። ምንም እንኳ ትዕቢተኞች በሐሰት ስሜን ቢያጠፉ እኔ ትእዛዞችህን በሙሉ ልቤ እጠብቃለሁ። እነርሱ ትዕቢተኞችና ስሜተ ቢሶች ናቸው፤ እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል። ሕግህን እንድማር ስላደረገኝ መቀጣቴ መልካም ሆነልኝ። ከብዙ ወርቅና ከብዙ ብር ይልቅ ለእኔ እጅግ ዋጋ ያለው አንተ የምትሰጠው ሕግ ነው።
መጽሐፈ መዝሙር 119 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መዝሙር 119:1-72
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos