መጽሐፈ መዝሙር 118
118
ስለ ድል አድራጊነት የቀረበ የምስጋና ጸሎት
1ቸር ስለ ሆነና ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ስለ ሆነ
እግዚአብሔርን አመስግኑ። #1ዜ.መ. 16፥34፤ 2ዜ.መ. 5፥13፤ 7፥3፤ ዕዝ. 3፥11፤ መዝ. 100፥5፤ 106፥1፤ 107፥1፤ 136፥1፤ ኤር. 33፥11።
2የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ
“የእግዚአብሔር ፍቅር ዘለዓለማዊ ነው” ይበሉ።
3የእግዚአብሔር ካህናት የሆኑት የአሮን ልጆች ሁሉ
“የእግዚአብሔር ፍቅር ዘለዓለማዊ ነው” ይበሉ።
4የሚፈሩት ሁሉ
“የእግዚአብሔር ፍቅር ዘለዓለማዊ ነው” ይበሉ።
5በተጨነቅሁ ጊዜ ጩኸቴን ወደ
እግዚአብሔር አሰማሁ፤
እርሱም ሰማኝ፤ ነጻም አወጣኝ።
6እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ሆኖ ስለሚረዳኝ አልፈራም፤
ከቶ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል? #ዕብ. 13፥6።
7እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ሆኖ ስለሚረዳኝ፥
የጠላቶቼን ውድቀት አያለሁ።
8በሰው ከመመካት ይልቅ
በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል።
9በመሪዎች ከመመካት ይልቅ፥
በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል።
10ብዙ ሕዝቦች ከበውኝ ነበር፤
ነገር ግን በእግዚአብሔር ኀይል ደመሰስኳቸው።
11ከየአቅጣጫው በዙሪያዬ ነበሩ፤
ነገር ግን በእግዚአብሔር ኀይል ደመሰስኳቸው።
12ዙሪያዬን እንደ ንብ ከበቡኝ፤
ነገር ግን እሾኽ በእሳት እንደሚቃጠል
በፍጥነት ተቃጠሉ፤
በእግዚአብሔርም ኀይል ደመሰስኳቸው።
13ብርቱ ጥቃት ደርሶብኝ፥
ለመውደቅ ተቃርቤ ነበር፤
ነገር ግን እግዚአብሔር ረዳኝ።
14እግዚአብሔር ከለላዬና መከላከያዬ ነው፤
አዳኜም እርሱ ነው። #ዘፀ. 15፥2፤ ኢሳ. 12፥2።
15በጻድቃን ድንኳን ውስጥ
እንዲህ የሚል የድል አድራጊነት
ድምፅ ይሰማል፦
“የእግዚአብሔር ኀይል ያሸንፋል!”
16የእግዚአብሔር ኀይል ከፍ ከፍ አለ፤
ኀይሉም ድል አድራጊ ነው።
17በሕይወት እኖራለሁ እንጂ አልሞትም፤
የእግዚአብሔርንም ድንቅ ሥራ ዐውጃለሁ።
18በብርቱ ቀጥቶኛል፤
ነገር ግን እንድሞት አላደረገኝም።
19ወደ ውስጥ ገብቼ እግዚአብሔርን እንዳመሰግን
የቤተ መቅደስን በሮች ከፈቱልኝ።
20ይህ የእግዚአብሔር በር ነው፤
ጻድቃን በእርሱ ይገባሉ።
21እግዚአብሔር ሆይ!
ስለ ሰማኸኝና ስላዳንከኝ አመሰግንሃለሁ።
22ግንበኞች የናቁት ድንጋይ
እርሱ ዋና የማእዘን ራስ ሆነ። #ሉቃ. 20፥17፤ ሐ.ሥ. 4፥11፤ 1ጴጥ. 2፥7።
23ይህም የእግዚአብሔር ሥራ ነው፤
ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው። #ማቴ. 21፥42፤ ማር. 12፥10-11።
24ይህ እግዚአብሔር የሠራው የድል ቀን ነው፤
በእርሱ ደስ ይበለን፤ ሐሴትም እናድርግ!
25እግዚአብሔር ሆይ! እባክህ አድነን!
እግዚአብሔር ሆይ! እባክህ ሁሉ ነገር የተሟላ እንዲሆን አድርግልን! #ማቴ. 21፥9፤ ማር. 11፥9፤ ዮሐ. 12፥3።
26በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ይሁን!
በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሆነን
እንባርካችኋለን። #ማቴ. 21፥9፤ 23፥39፤ ማር. 11፥9፤ ሉቃ. 13፥35፤ 19፥38፤ ዮሐ. 12፥13።
27እግዚአብሔር አምላክ ነው፤
ብርሃንን ሰጥቶናል፤
ለምለም የሆኑ ቅርንጫፎችን ይዘን በዓል ለማክበር
ወደ መሠዊያው እንሂድ።
28አንተ አምላኬ ስለ ሆንክ አመሰግንሃለሁ፤
ታላቅነትህንም ዐውጃለሁ።
29ቸር ስለ ሆነና ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ስለ ሆነ፥
እግዚአብሔርን አመስግኑት።
Currently Selected:
መጽሐፈ መዝሙር 118: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997