መጽሐፈ መዝሙር 109:1-13

መጽሐፈ መዝሙር 109:1-13 አማ05

የማመሰግንህ አምላክ ሆይ፥ እባክህ ዝም አትበል። ክፉዎችና ሐሰተኞች ተቃውመውኛል፤ በእኔ ላይ በሐሰት ይናገራሉ። በጥላቻ ዙሪያዬን ከበቡኝ፤ ያለ ምክንያትም አደጋ ጣሉብኝ ለወዳጅነቴ የመለሱልኝ አጸፋ ክስ ነው፤ እኔ ግን እጸልይላቸዋለሁ። በመልካም ፈንታ ክፉ፥ በፍቅር ፈንታ ጥላቻ ይመልሱልኛል። በእርሱ ላይ የሚፈርድ ዐመፀኛ ዳኛ ሠይም አንዱም ሰው እንዲከስሰው አድርግ፤ በተሟገተ ጊዜ ተረትቶ ይመለስ፤ ጸሎቱ እንኳ እንደ ኃጢአት ይቈጠርበት፤ ዕድሜውም በቶሎ ይቀጭ፤ ሥራውንም ሌላ ሰው ይውሰድበት። ልጆቹ ያለ አባት ይቅሩ፤ ሚስቱም ባልዋ የሞተባት ሴት ትሁን። ልጆቹ ቤት የሌላቸው ለማኞች ይሁኑ፤ አሁን ከሚኖሩበት ፍርስራሽ ቤት እንኳ ይባረሩ። ንብረቱ ሁሉ በዕዳ ይያዝበት፤ ለፍቶ ያገኘውን ጥሪት ሁሉ ባዕዳን ሰዎች ይውሰዱበት። የሚራራለት ሰው ከቶ አይኑር፤ ድኻ ዐደግ ልጆቹን የሚንከባከባቸው ሰው አይገኝ። ለስሙ መጠሪያ የሚሆን አንድ ልጅ እንኳ አይቅርለት፤ ከአንድ ትውልድ በኋላ የሚያስታውሰው አይኑር።