የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መዝሙር 106:16-33

መጽሐፈ መዝሙር 106:16-33 አማ05

በበረሓ ሰፍረው ሳሉ በሙሴና የእግዚአብሔር ቅዱስ አገልጋይ በሆነው በአሮን ቀኑባቸው። ምድርም ተከፍታ ዳታንን ዋጠች፤ አቤሮንንና ቤተሰቡንም ከደነቻቸው። በተከታዮቻቸውም ላይ እሳት ወረደ፤ እነዚያንም ክፉ ሰዎች አቃጠለ። በኮሬብ ሳሉ የወርቅ ጥጃ ሠሩ፤ ለዚያም ጣዖት ሰገዱ። የእግዚአብሔርንም ክብር ሣር በሚበላ እንስሳ ምስል ለወጡ። በግብጽ ሳሉ ታላላቅ ተአምራትን በማድረግ ያዳናቸውን አምላክ ረሱ። በዚያ ሳሉ ያደረገላቸውን አስደናቂ ነገሮችና፥ በቀይ ባሕርም ያደረገላቸውን አስገራሚ ነገሮች ዘነጉ። ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ሕዝቦቹን ለማጥፋት ዐቅዶ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የመረጠው ሙሴ በመካከል በመቆም፥ እንዳያጠፋቸውና ቊጣውንም እንዲመልስ እግዚአብሔርን ለመነ። በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ስላልተማመኑ መልካሚቷን ምድር ናቁ። በድንኳኖቻቸው ውስጥ ሆነው አጒረመረሙ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል አንሰማም አሉ። ስለዚህ እጁን አንሥቶ በመማል በበረሓ የሚያጠፋቸው መሆኑን ነገራቸው፤ ዘሮቻቸውን ሁሉ በአሕዛብ መካከል እንደሚጥላቸውና በመላው ዓለም እንደሚበታትናቸው ገለጠላቸው። ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ሕዝብ በፔዖር የነበረውን ባዓል ተብሎ የሚጠራውን ጣዖት አመለኩ፤ ሕይወት ለሌላቸው አማልክት የቀረበውንም የመሥዋዕት ሥጋ በሉ። በክፉ ሥራቸው እግዚአብሔርን አስቈጡት፤ በዚህ ምክንያት መቅሠፍት በመካከላቸው ተነሣ። ነገር ግን ፊንሐስ ተነሥቶ በደል የፈጸሙትን በቀጣቸው ጊዜ መቅሠፍቱ ተወገደ። ይህም አድራጎቱ ወደ ፊት ለሚከተለው ትውልድ ለዘለዓለም እንደ መልካም ሥራ ሆኖ ተቈጠረለት። በመሪባ ምንጮች አጠገብ ሕዝቡ እግዚአብሔርን አስቈጡት፤ በእነርሱም ምክንያት ሙሴ ችግር ላይ ወደቀ። እጅግ አስመርረውት ስለ ነበር ሙሴ ራሱን ባለመቈጣጠር ተናገረ።