የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ምሳሌ 8

8
ስለ ጥበብ የቀረበ ውዳሴ
1አድምጡ! ጥበብ ትጣራለች፤
ማስተዋልም ድምፅዋን ታሰማለች።
2በመንገድ አጠገብ በሚገኙ ኰረብቶችና
በመንገድ መገናኛዎች ላይ ትቆማለች፤
3በከተማው መግቢያ በሮች ላይ ሆና እንዲህ ስትል ትጮኻለች፤ #ምሳ. 1፥20-21።
4“ሰዎች ሆይ! እናንተን ሁሉ እጠራለሁ፤
ወደ ሰው ዘር ሁሉ እጣራለሁ፤
5እናንተ ዕውቀት የሌላችሁ፥ ዕውቀትን ለመገብየት ተማሩ፤
እናንተ ሞኞች፥ ማስተዋልን ገንዘብ አድርጉ።
6የምናገረው ቁም ነገር ስላለኝ አድምጡ፤
ከአንደበቴ ትክክለኛ ነገር ይወጣል።
7እኔ እውነት የሆነውን እናገራለሁ፤
ክፋት በእኔ ዘንድ የተጠላ ነው።
8እኔ የምናገረው ሁሉ እውነት ነው፤
ጠማማ ወይም ወልጋዳ አይደለም።
9ማስተዋል ላለው ሰው ሁሉም ግልጥ ነው፤
ዕውቀትም ላለው ሰው ትክክል ነው።
10ከብር ይልቅ ምክሬን ምረጡ፤
ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ ዕውቀትን ምረጡ።
11“እኔ ጥበብ፥ ከዕንቊ የምበልጥ ስለ ሆንኩ
ምንም ነገር ብትመኙ ከእኔ የሚወዳደር አንድም ነገር የለም።
12እኔ ጥበብ፥ ማስተዋል አለኝ፤
ዕውቀትና ትክክለኛ አስተያየት የእኔ ናቸው።
13ክፉ ነገርን መጥላት እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤
እኔ ትዕቢትንና ዕብሪትን እጠላለሁ፤
ክፉ መንገድንና ጠማማ ንግግርን አልወድም
14ምክርና መልካም ጥበብ ከእኔ ይገኛሉ፤
ማስተዋልና ብርታትም የእኔ ናቸው።
15በእኔ አማካይነት ነገሥታት ይገዛሉ።
ሹማምንትም ትክክለኛ ሕግን ያዘጋጃሉ።
16በእኔ አጋዥነት መሪዎች ይገዛሉ።
መኳንንትም አገርን ያስተዳድራሉ።
17እኔ የሚወዱኝን እወዳለሁ፤
የሚፈልጉኝም ያገኙኛል።
18ብልጽግናና ክብር በእኔ ዘንድ ይገኛሉ፤
ዘላቂ ሀብትና ዕድገት የእኔ ናቸው።
19ከእኔ የምታገኙት ጥቅም ዘላቂ ሀብትና ዕድገት የእኔ ናቸው።
ከንጹሕ ወርቅና ከተነጠረ ብር የሚሻል ነው።
20የእኔ መንገድ የጽድቅ መንገድ ነው፤
እኔ የምከተለው የፍትሕን ፈለግ ነው።
21ለሚወዱኝ ሀብትን እሰጣቸዋለሁ፤
ቤታቸውንም በብልጽግና እሞላዋለሁ።
22“እግዚአብሔር ከሁሉ በፊት ፈጠረኝ፤
ከጥንት ጀምሮ የሥራው ተቀዳሚ አደረገኝ። #ራዕ. 3፥14።
23ዓለም ከመፈጠርዋ አስቀድሞ፥
ከዘመናት በፊት ተሾምኩ።
24የውሃ ምንጮች ከመፍለቃቸው፥
ውቅያኖሶችም ከመገኘታቸው በፊት ተወለድኩ።
25ተራራዎችና ኰረብቶች ከመመሥረታቸው በፊት ተወለድኩ።
26እግዚአብሔር ምድርን ሁሉ ከመፍጠሩ በፊት፥
ወይም የመጀመሪያው ዐፈር እንኳ ከመፈጠሩ በፊት ተወለድኩ።
27እግዚአብሔር ሰማይን በዘረጋ ጊዜ፥
ጠፈርንም ከውቅያኖሶች በላይ ባዘጋጀ ጊዜ፥
እኔ እዚያ አብሬው ነበርኩ።
28ደመናትን በጠፈር ባኖረበት ጊዜ፥
የውቅያኖስን ምንጭ በከፈተ ጊዜ፥
29የባሕር ውሃዎች ከተመደበላቸው ስፍራ በላይ ከፍ እንዳይሉ ባዘዛቸው ጊዜ፥
የምድርን መሠረት ባጸና ጊዜ
እኔ እዚያ አብሬው ነበርኩ።
30በዚያን ጊዜ እንደ ዋና ሠራተኛ ሆኜ ከእርሱ ጋር ነበርኩ።
ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበር።
እኔም በፊቱ እደሰት ነበር።
31እርሱ በፈጠረው ዓለም ደስ ይለኛል፤
በሰው ዘርም ሐሤት አደርጋለሁ።
32“ልጆቼ ሆይ! አድምጡኝ
መንገዴን የሚከተሉ ይደሰታሉ።
33የምትማሩትን አስተውሉ፤
ብልኆች ሁኑ፤ ቸልም አትበሉት።
34እኔን የሚያዳምጥ፥
በየቀኑ በደጃፌ ላይ ተግቶ የሚገኝ፥
በቤቴ መግቢያ አጠገብ የሚጠባበቀኝ ሰው የተባረከ ነው።
35እኔን የሚያገኝ፥ ሕይወትን ያገኛል፤
ከእግዚአብሔርም ሞገስን ያገኛል።
36እኔን ያጣ ራሱን ይጐዳል፤
እኔን የሚጠላም ሞትን ይወዳል።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ