መጽሐፈ ምሳሌ 7
7
1ልጄ ሆይ! ቃሌን ጠብቅ፤ ትእዛዞቼንም በልብህ ውስጥ አኑር። 2በሕይወት እንድትኖር ትእዛዞቼን ጠብቅ፤ የማስተምርህንም ሁሉ እንደ ዐይንህ ብሌን ጠብቅ፤ 3እንደ ጣትህ ቀለበት ጠብቃቸው፤ በልብህም ሰሌዳ ቅረጻቸው። 4ጥበብን እንደ እኅትህ፥ ማስተዋልንም እንደ ቅርብ ወዳጅህ አድርገህ ቊጠራቸው። 5እነርሱ ከአመንዝራ ሴት እንድትርቅና ከሌላ ሰው ሚስት አሳሳች ቃል እንድትጠበቅ ያደርጉሃል።
የአመንዝራ ሴት አታላይነት
6ከዕለታት አንድ ቀን በቤቴ መስኮት ወደ ውጪ እመለከት ነበር፤ 7ዕውቀት ከጐደላቸው ሰዎች መካከል ወጣቶችን ተመለከትኩ፤ ከእነርሱም መካከል አስተሳሰብ የጐደለው አንድ ወጣት አየሁ። 8አንዲት ሴት በምትኖርበት ቤት አጠገብ ባለው መንገድ ማእዘን ያልፍ ነበር፤ ወደ ቤትዋም አቅጣጫ ይራመድ ነበር፤ 9ይህንንም ያደርግ የነበረው ወደ ማታ ጊዜ ጨለምለም ሲል ነበር፤ 10ከዚያም በኋላ ሴትዮዋ ወጣችና አገኘችው፤ አለባበስዋም ሴትኛ ዐዳሪ መሆኗን ያመለክት ነበር፤ ሰውንም የምታስትበት ዕቅድ ነበራት። 11እርስዋ ደፋርና ኀፍረተቢስ ሴት ነበረች፤ በቤትዋ መቀመጥ ስለማያስደስታት ዘወትር ትዞራለች፤ 12በየማእዘኑ፥ በየመንገዱና በየገበያ ስፍራ እየቆመች ትጠባበቃለች። 13ያንን ወጣት ዕቅፍ አድርጋ ሳመችው፤ ያለ ኀፍረት እንዲህ አለችው፦ 14“እኔ መሥዋዕት ማቅረብ ነበረብኝ፤ ዛሬ የስእለቴን መባ አቅርቤአለሁ፤ 15ስለዚህ አንተን ለመቀበል ወጣሁ፤ በብርቱም ፈለግኹህ፤ እነሆም አገኘሁህ! 16ከግብጽ አገር የመጣውን ጌጠኛ አንሶላ በአልጋዬ ላይ አንጥፌአለሁ። 17ከርቤ አልሙንና ቀረፋ ከተባሉት ቅመሞች የተሠራ ሽቶ አርከፍክፌበታለሁ። 18ና ሌሊቱን ሙሉ በፍቅር እንርካ፤ በመተቃቀፍም ደስ ይበለን! 19ባሌ በቤት የለም፤ ወደ ሩቅ አገር ሄዶአል፤ 20ብዙ ገንዘብ ይዞ ስለ ሄደ እስከ ሁለት ሳምንት አይመለስም።” 21በሚማርኩ ቃሎችዋ አግባባችው፤ በለዘበ አነጋገርዋም አታለለችው። 22በሬ ወደሚታረድበት ስፍራ እንደሚነዳ፥ አጋዘንም ቸኲሎ ወደ ወጥመድ እንደሚገባ፥ ወዲያውኑ እርስዋን ተከትሎ ሄደ፤ 23ፍላጻም ሆድ ዕቃውን እንደሚወጋው ዐይነት ሆነ፤ ወደ ወጥመድ እንደሚገባ ወፍ መሰለ፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ሕይወቱ በአደጋ ላይ ለመውደቅ መቃረቡን አላወቀም።
24እንግዲህ ልጄ ሆይ! አድምጠኝ፤ የምልህንም በጥንቃቄ ስማ፤ 25እንደዚህ ዐይነትዋ ሴት ልብህን እንድትማርክ አታድርጋት፤ የእርስዋንም መንገድ በመከተል አትሳሳት። 26እርስዋ ለብዙ ሰዎች የመጥፊያ ምክንያት ሆናለች፤ እጅግ ብዙ ሰዎች በእርስዋ ተማርከው ጠፍተዋል። 27ወደ እርስዋ ቤት የሚወስደው መንገድ ወደ ሞትና ወደ መቃብር የሚያወርድ ጐዳና ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 7: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997