መጽሐፈ ምሳሌ 30
30
አጉር የተናገራቸው ነገሮች
1የማሳ አገር ሰው የያቄ ልጅ አጉር በጥሞና የተናገራቸው ንግግሮች የሚከተሉት ናቸው፦
“አምላክ ሆይ! ደክሜአለሁ፤
አምላክ ሆይ! ደክሜአለሁ፤
እንዴት ልቋቋመው እችላለሁ?
2ከሰውነት ደረጃ ወጥቼ እንደ እንስሳ ሆኛለሁ፤
ሰው ሊኖረው የሚገባው ማስተዋል የለኝም።
3ከቶ ጥበብን አልተማርኩም፤
ስለ እግዚአብሔር የማውቀው ምንም ነገር የለኝም።
4ወደ ሰማይ ወጥቶ የወረደ ማን ነው?
ነፋስን በእጁ የጨበጠ፥
ውሃን በልብሱ የቋጠረ፥
የምድርን ዳርቻ ያጸና ማን ነው?
የሰውዬው ስም ማነው?
የልጁስ ስም ማን ይባላል?
ታውቅ እንደሆን ንገረኝ፤
5“እግዚአብሔር የሚናገረው ቃል ሁሉ እውነት ነው፤ ለሚታመኑበት ሁሉ ጋሻ ነው። 6እርሱ ያላለውን ብሎአል ብትል ይገሥጽሃል፤ ሐሰተኛ መሆንህንም ይገልጣል።”
ሌሎች ምሳሌዎች
7አምላክ ሆይ! ከመሞቴ በፊት የሚከተሉትን ሁለት ነገሮች እንዳትነሣኝ እለምንሃለሁ፦
8ሰውን ከማታለልና ሐሰት ከመናገር ጠብቀኝ፤ የሚያስፈልገኝን ያኽል ምግብ ስጠኝ እንጂ ሀብታም ወይም ድኻ አታድርገኝ።
9ብዙ ሀብት ቢኖረኝ “እግዚአብሔር ማን ነው?” ብዬ አንተን እስከ መካድ እደርሳለሁ፤ ድኻ ብሆን ደግሞ እሰርቅ ይሆናል፤ በዚህም ሁኔታ የአንተን የአምላኬን ስም አሰድባለሁ።
10እንዳትረገምና መከራ ላይ እንዳትወድቅ አገልጋይን ባሳዳሪው ፊት አትንቀፈው።
11አባቶቻቸውን የሚሰድቡ፥ እናቶቻቸውንም የማያመሰግኑ ሰዎች አሉ።
12በጣም የረከሱ ሆነው ሳለ ንጹሕ የሆኑ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ።
13በትዕቢት የተሞሉና ሰውን የሚንቁ ሰዎች አሉ።
14ጥርሳቸው እንደ ሰይፍ፥ መንጋጋቸው እንደ ካራ የሆኑ ድኾችንና ችግረኞችን በግፍ የሚበዘብዙ ሰዎች አሉ።
15አልቅት “ስጠኝ! ስጠኝ!” እያሉ የሚጮኹ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉአት፤
እንዲሁም ከቶ የማይጠግቡና በቃን የማይሉ ሦስት ነገሮች አሉ፤ እንዲያውም አራት ናቸው፤ 16እነርሱም፦
“መቃብር፥ መኻን ሴት፥
ዝናብ የሚያስፈልገው ደረቅ ምድርና
ከቊጥጥር ውጪ የሆነ የእሳት ቃጠሎ” ናቸው።
17በአባቱ የሚያፌዝና እናቱ በምታረጅበት ጊዜ የሚንቃት ሰው የሸለቆ ቊራዎች ዐይኖቹን ጐጥጒጠው ያወጡታል፤ ጆፌ አሞራዎችም ይበሉታል።
18ላስተውላቸው የማልችል እጅግ ምሥጢር የሆኑ ሦስት ነገሮች አሉ፤ እንዲያውም አራት ናቸው።
19እነርሱም፦
“በሰማይ የሚበር ንስር፥
በአለት ላይ የሚጐተት እባብ፥
በባሕር ላይ የሚጓዝ መርከብና
ከሴት ጋር ፍቅር የያዘው ወንድ” ናቸው።
20የማትታመን ሚስት ሁኔታም እንዲሁ ነው፤ እርስዋ በባልዋ ላይ ታመነዝርና ንጹሕ ሰው በመምሰል “ምንም በደል አልፈጸምኩም” ትላለች።
21በሦስት ነገሮች ምክንያት ምድር ትንቀጠቀጣለች፤ ልትታገሥም አትችልም፤ እንዲያውም አራት ናቸው፤
22እነርሱም “ባሪያ ሲነግሥ፥ ቦዘኔ ሲጠግብ፥
23የተጠላች ሴት ባል ስታገባና፥
ሴት ባሪያ እመቤትዋን ስትወርስ” የሚከሠቱ ሁኔታዎች ናቸው።
24በዓለም ላይ በብልኅነታቸው የታወቁ አራት ትንንሽ ፍጥረቶች አሉ፤
25ጒንዳኖች፦ ጒንዳኖች ደካሞች ናቸው፤
ነገር ግን በበጋ ጊዜ ምግባቸውን ያከማቻሉ።
26ሽኮኮዎች፦ ሽኮኮዎች ብርቱዎች አይደሉም፤
ነገር ግን መኖሪያቸውን በአለቶች መካከል ይሠራሉ።
27አንበጦች፦ አንበጦች ንጉሥ የላቸውም፤
ነገር ግን ሁሉም በሥነ ሥርዓት ይጓዛሉ።
28እንሽላሊቶች፦ እንሽላሊቶች በእጅ ስለሚያዙ ቀላል ፍጥረቶች መስለው ቢታዩም፥
በቤተ መንግሥት እንኳ ሳይቀር በሁሉ ስፍራ ይገኛሉ።
29አረማመዳቸው አስደሳች የሆነ ሦስት ነገሮች አሉ፤ እንዲያውም አራት ናቸው፤
30እነርሱም፥ በእንስሶች መካከል ብርቱ የሆኑና ከማንም ፊት የማይሸሹ አንበሶች፥
31አውራ ፍየሎች፥ የሚንጐራደዱ አውራ ዶሮዎች፥
በሕዝቦቻቸው ፊት በክብር የሚታዩ ነገሥታት ናቸው።
32ሞኝነትህ ትምክሕተኛ እንድትሆን ቢያደርግህና ክፉ ነገር ለማድረግ ብታቅድ፥ ቆም ብለህ አስብ።
33ወተት ቢናጥ ቅቤ ያስገኛል፤
የሰው አፍንጫ ቢጠመዘዝ ይደማል፤
ቊጣ ቢነሣሣ ጠብን ያመጣል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ምሳሌ 30: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997