የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ምሳሌ 19

19
1በንግግሩ ከሚቀላምድ ሞኝ ሰው ይልቅ
በቅንነት የሚኖር ድኻ ሰው ይሻላል።
2ዕውቀት ያልተጨመረበት ትጋት ጠቃሚ አይደለም፤
በችኰላ የሚሮጥ ሰው መንገዱን ይስታል።
3አንድ ሰው በሞኝነቱ ጥፋት ሲደርስበት
በእግዚአብሔር ላይ ያማርራል።
4ሰው በሀብቱ ብዙ ወዳጆችን ያፈራል፤
ድኾችን ግን ያሉአቸው ጥቂት ወዳጆች እንኳ ይከዱአቸዋል።
5በሐሰት የሚመሰክር ሰው ሳይቀጣ አይቀርም፤
ሐሰት የሚናገር ከቅጣት አያመልጥም።
6ብዙ ሰዎች የለጋሥ ሰውን ወዳጅነት ይፈልጋሉ፤
ስጦታን ለሚሰጥ ሰው ሁሉም ወዳጁ ነው።
7ድኻን የገዛ ወንድሞቹ እንኳ ይጠሉታል፤
ወዳጆቹማ የበለጠ ያርቁታል፤
የቱንም ያኽል ቢጣጣር ወዳጆች አይኖሩትም።
8ጥበብን የሚገበይ ሰው ራሱን ይወዳል፤
ዕውቀትን አጥብቆ የሚይዝ ይበለጽጋል።
9በሐሰት የሚመሰክር ሰው ሳይቀጣ አይቀርም፤
ሐሰትንም የሚናገር ጥፋት ያገኘዋል።
10ሞኞች በድሎት መኖር አይችሉም፤
የባሪያ በመኳንንት ላይ ገዢ መሆንማ ምንኛ የከፋ ነው?
11የቊጣን ስሜት መቈጣጠር አስተዋይነት ነው፤
ለበደለም ይቅርታ ማድረግ ጨዋነት ነው።
12የንጉሥ ቊጣ እንደ አንበሳ ጩኸት አስፈሪ ነው፤
ከንጉሥ ዘንድ የሚገኝ ሞገስ ግን
ሣርን እንደሚያለመልም ጠል ነው።
13ሞኝ ልጅ አባቱን ወደ ጥፋት ያደርሳል፤
ጨቅጫቃ ሚስትም እንደማያቋርጥ ዝናብ አሰልቺ ናት።
14አንድ ሰው ቤትና ሀብት ከወላጆቹ ሊወርስ ይችላል፤
አስተዋይ ሚስትን የሚሰጥ ግን እግዚአብሔር ብቻ ነው።
15ስንፍና እንቅልፍን ያስከትላል፤
ስለዚህም ሰነፍ ሰው ይራባል።
16ትእዛዝን የሚጠብቅ በሕይወት ይኖራል፤
የእግዚአብሔርን ቃል የሚንቅ ግን ይጠፋል።
17ለድኾች የሚሰጥ ለእግዚአብሔር እንዳበደረ ይቈጠራል፤
እግዚአብሔርም የመልካም ሥራውን ዋጋ ይከፍለዋል።
18የመመለስ ተስፋ ሳላቸው ልጆችህን በልጅነታቸው ቅጣቸው፤
ባትቀጣቸው ግን ለጥፋት አሳልፈህ እንደ ሰጠሃቸው ይቈጠራል።
19ግልፍተኛ ሰው ቢኖር የግልፍተኛነቱን ዋጋ እንዲያገኝ ተወው፤
አንድ ጊዜ ከችግሩ ልታወጣው ብትሞክር
ሌላ ጊዜም እንዲሁ ማድረግህ አይቀርም።
20ምክርን ብትሰማና ለመማርም ፈቃደኛ ብትሆን
የኋላ ኋላ ጥበብ መገብየትህ አይቀርም።
21ሰዎች ብዙ ነገር ያቅዳሉ፤
ተፈጻሚነትን የሚያገኘው ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው።
22ከሰው የሚፈለገው ታማኝነት ነው፤
ሐሰተኛ ከመሆን ይልቅ ድኻ መሆን ይሻላል።
23እግዚአብሔርን ብትፈራ ረጅም ዕድሜ ይኖርሃል፤
ጒዳት ሳይደርስብህ በደስታና በሰላም ትኖራለህ።
24አንዳንድ ሰዎች በጣም ሰነፎች ናቸው፤
ሌላው ቀርቶ በወጥ ያጠቀሱትን እንጀራ መጒረስ ይታክታቸዋል።
25ፌዘኛ ብትቀጣው አላዋቂው ብልኅ ይሆናል፤
አስተዋይ ሰው ብትገሥጸው የበለጠ ዕውቀትን ይጨምራል።
26አሳፋሪና አስነዋሪ የሆነ ልጅ አባቱን ያጒላላል፤
እናቱንም ከቤት ያባርራል።
27ልጄ ሆይ! ምክሬን ባትሰማ
የምታውቀውን ትምህርት እንኳ በቶሎ ረስተህ ትሳሳታለህ።
28ሌላውን ሰው ለመበደል
በሐሰት የሚመሰክር ሰው ካለ
ፍትሕ ይጓደላል።
ዐመፀኞችም ክፋት ማድረግ ያበዛሉ።
29ለፌዘኞች ፍርድ፥
ለሞኞችም ግርፋት ተዘጋጅቶላቸዋል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ