የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ምሳሌ 18

18
1ራስ ወዳድ ሰው የራሱን ምኞት ብቻ ይከተላል፤
ከሌላ ሰው የሚቀርብ ትክክለኛ አስተሳሰብን እንኳ ይቃወማል።
2ሞኝ የራሱን አስተያየት ብቻ መግለጥ ይፈልጋል እንጂ
ዕውቀትን ከሌላ ሰው መገብየት ደስ አያሰኘውም።
3ኃጢአትና ውርደት የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው፤
ክብርህን ብታጣ በምትኩ የምታገኘው ውርደት ነው።
4ከሰው አንደበት የሚወጣው የጥበብ ንግግር
እንደ ጥልቅ ውሃ ነው፤
እንደ ምንጭ ውሃም ጣፋጭ ነው።
5ለበደለኛው ማዳላትና
ንጹሕ ሰው ትክክለኛ ፍትሕ እንዳያገኝ
ማድረግ ተገቢ አይደለም።
6የሞኝ ንግግር ጠብን ያነሣሣል፤
ልፍለፋውም በትርን ይጋብዛል።
7ሞኝ በሚናገርበት ጊዜ ራሱን በጒዳት ላይ ይጥላል፤
አነጋገሩም ወጥመድ ሆኖ ይይዘዋል።
8የሐሜተኛ ሰው ቃል እንደ ጣፋጭ ምግብ ደስ እያሰኘ
እስከ ውስጥ ሰውነት ድረስ ይወርዳል።
9ሰነፍ ሰው ከአጥፊ ሰው ተለይቶ አይታይም፤
10የእግዚአብሔር ስም እንደ ጠንካራ ምሽግ ነው፤
ስለዚህ ደጋግ ሰዎች ወደ እርሱ ተጠግተው ይድናሉ።
11ሀብታሞች ግን ሀብታቸው በከተማ ዙሪያ እንዳለ ከፍተኛና
ጠንካራ ግንብ የሚጠብቃቸው ይመስላቸዋል።
12ትዕቢት ጥፋትን ያመጣል፤
ትሕትና ግን ክብርን ያጐናጽፋል።
ክብርን ግን ትሕትና ይቀድመዋል።
13ሳያዳምጡ መልስ መስጠት፥
ሞኝ ያደርጋል፤ አሳፋሪም ነው።
14ጠንካራ መንፈስ ሕመምን ያስታግሣል፤
መንፈሱ የደከመውን ግን ማንም አይረዳውም።
15የጥበበኛ ሰው ልብ ዕውቀትን ገንዘብ ያደርጋል፤
የአስተዋዮችም ጆሮ ጥበብን ይፈልጋል።
16ስጦታ ለሰጪው መንገድን ይከፍትለታል፤
ወደ ትልልቆች ሰዎችም ፊት መቅረብ ያስችለዋል።
17በአደባባይ በመጀመሪያ ቀርቦ የሚናገር ሰው
ተከራካሪው መጥቶ ጥያቄ እስከሚያቀርብለት ድረስ፥
ዘወትር እርሱ ብቻ ትክክል የሆነ ይመስለዋል።
18ዕጣ መጣል ጠብን ያበርዳል፤
ሁለት ጠንካራ ተከራካሪዎችንም ይገላግላል።
19ወንድምህን እርዳው፤
እርሱም በከተማ ዙሪያ እንዳለ ጠንካራ ግንብ ይጠብቅሃል፤
ከእርሱ ጋር ብትጣላ ግን በሩን ይዘጋብሃል።
20ሰው በሚናገረው የንግግር ውጤት
በመርካት ተደስቶ ይኖራል።
21አንደበትህ ሕይወትህን ሊያድን ወይም ሊያጠፋ ይችላል፤
ስለዚህ በአንደበትህ ወዳጆችን ብታፈራ ተደስተህ ትኖራለህ።
22ሚስት ከእግዚአብሔር የምትሰጥ በረከት ስለ ሆነች
ሚስት ካገኘህ መልካም ነገር አግኝተሃል ማለት ነው፤
23ድኻ እየተለማመጠ በትሕትና ይናገራል፤
ሀብታም ግን በትምክሕት ይመልሳል።
24ወዳጆች ሳይሆኑ ወዳጆች መስለው የሚታዩ አሉ፤
እውነተኛ ወዳጅ ግን ከወንድም ይበልጣል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ