የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 9:15-23

ኦሪት ዘኊልቊ 9:15-23 አማ05

የመገናኛው ድንኳን በተተከለበት ቀን ደመናው ድንኳኑን ሸፈነው፤ ከማታ ጀምሮ እስከ ጠዋት ድረስ በድንኳኑ ላይ እንደ እሳት ያበራ ነበር፤ በቀን ደመና ይሸፍነው ነበር፤ ደመናውም በሌሊት እንደ እሳት ያበራ ነበር። ደመናው ከድንኳኑ ላይ በሚነሣበት ጊዜ ሁሉ እስራኤላውያን ሰፈራቸውን ለቀው ይጓዙ ነበር፤ ደመናውም በሚወርድበት ቦታ እንደገና ይሰፍሩ ነበር፤ እስራኤላውያንም ከሰፈር የሚለቁትም ሆነ በሌላ ቦታ የሚሰፍሩት በእግዚአብሔር ትእዛዝ ነበር፤ ደመናው በድንኳኑ ላይ ዐርፎ እስከ አለ ድረስ በአንድ ሰፈር ይቈያሉ፤ ደመናው በድንኳኑ ላይ ለብዙ ቀኖች ቢቈይ እንኳ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ እዚያው ይቈያሉ እንጂ አይንቀሳቀሱም። አንዳንድ ጊዜ ደመናው በድንኳኑ ላይ የሚቈይ ለጥቂት ቀኖች ብቻ ነበር፤ ያም ሆነ ይህ በሰፈር የሚቈዩትም ሆነ ወደ ፊት የሚሄዱት በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት ነበር፤ አንዳንድ ጊዜ ደመናው የሚቈየው ከምሽት እስከ ንጋት ብቻ ነበር፤ ስለዚህ ደመናው እንደ ተነሣ ወዲያውኑ ጒዞ ይቀጥላሉ፤ ወይም ደመናው ቀንና ማታ ቢቈይ ደመናው ሲነሣ ይሄዱ ነበር። ሁለት ቀንም ይሁን አንድ ወር፥ አንድ ዓመትም ይሁን ከዚያ የረዘመ ጊዜ ደመናው በድንኳኑ ላይ እስካረፈበት ጊዜ ድረስ አይንቀሳቀሱም ነበር፤ ደመናው ሲነሣ ግን ጒዞአቸውን ይቀጥሉ ነበር። ድንኳናቸውን የሚተክሉትም ሆነ ሰፈር ለቀው ወደ ፊት የሚጓዙት እግዚአብሔር ለሙሴ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ነበር።