የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘኍልቍ 9:15-23

ዘኍልቍ 9:15-23 NASV

ማደሪያው በተተከለ ዕለት ደመናው የምስክሩን ድንኳን ሸፈነው፤ ከምሽት እስከ ንጋት ድረስ ማደሪያውን የሸፈነው ደመና እሳት ይመስል ነበር። ይህ በዚህ ሁኔታ ቀጠለ፤ ደመናው ማደሪያውን ሸፈነው፤ በሌሊትም የእሳት መልክ ነበረው። ደመናው ከድንኳኑ ላይ በሚነሣበት ጊዜ እስራኤላውያን ጕዟቸውን ይጀምሩ ነበር፤ ደመናው በሚቆምበት ቦታ ደግሞ ይሰፍሩ ነበር፤ እስራኤላውያን ጕዞ የሚጀምሩትም ሆነ የሚሰፍሩት በእግዚአብሔር ትእዛዝ ነበር። ደመናው በድንኳኑ ላይ በሚቈይበት ጊዜ ሁሉ ከሰፈር አይንቀሳቀሱም ነበር። ደመናው በድንኳኑ ላይ ብዙ ቀን ቢቈይም እስራኤላውያን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቃሉ እንጂ ተነሥተው አይጓዙም። አንዳንድ ጊዜ ደመናው በድንኳኑ ላይ የሚቈየው ለጥቂት ቀን ብቻ ነበር፤ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ይሰፍራሉ፤ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ጕዞ ይጀምራሉ፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ደመናው ከምሽት እስከ ንጋት ብቻ ይቈያል፤ ደመናው ንጋት ላይ ሲነሣም ጕዟቸውን ይጀምራሉ፤ ቀንም ይሁን ሌሊት ደመናው ከተነሣ ጕዞ ይጀምራሉ። ደመናው በድንኳኑ ላይ ለሁለት ቀንም ይሁን ለወር ወይም ለዓመት ቢቈይ፣ እስራኤላውያን በሰፈር ይቈያሉ እንጂ ጕዟቸውን አይቀጥሉም። በእግዚአብሔር ትእዛዝ ይሰፍራሉ፤ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ይጓዛሉ፤ እነርሱም በሙሴ አማካይነት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር።