ኦሪት ዘኊልቊ 8:15-26

ኦሪት ዘኊልቊ 8:15-26 አማ05

ካነጻሓቸውና ከቀደስካቸውም በኋላ ሌዋውያን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለማገልገል ብቃት ይኖራቸዋል። እኔ እነርሱን በኲር ሆነው ለሚወለዱት ለእስራኤላውያን ወንዶች ልጆች ሁሉ ምትክ አድርጌ ስለ መረጥኳቸው የእኔ ብቻ ይሆናሉ። በግብጽ ምድር በኲር ሆኖ የተወለደውን በገደልኩ ጊዜ ከእያንዳንዱ እስራኤላዊ ቤተሰብ በኲር ሆኖ የተወለደውንና የእንስሶችንም በኲር ሁሉ ለእኔ የተለየ እንዲሆን ቀድሼው ነበር። እነሆ፥ አሁን ግን ስለ እስራኤላውያን በኲር ልጆች ምትክ ሌዋውያንን ለይቻለሁ፤ የእስራኤልን ሕዝብ ወክለው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ እንዲያገለግሉና እስራኤላውያን ወደ ተቀደሰው ስፍራ በመቅረብ እንዳይቀሠፉ ይጠብቁአቸው ዘንድ፥ ሌዋውያንን ከእስራኤላውያን እንደ ስጦታ ተቀብዬ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጥቻለሁ።” ስለዚህ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት፥ ሙሴና አሮን እንዲሁም የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ሌዋውያንን ቀደሱ። ሌዋውያንም ራሳቸውን አነጹ፤ ልብሳቸውንም አጠቡ፤ አሮንም ለእግዚአብሔር ልዩ ስጦታ አድርጎ ለእግዚአብሔር ለያቸው የመንጻቱንም ሥርዓት ፈጸመላቸው፤ እግዚአብሔር ለሙሴ ስለ ሌዋውያን በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሕዝቡ ሁሉን ነገር አደረጉ፤ በዚህም ዐይነት ሌዋውያን በአሮንና በልጆቹ ኀላፊነት ሥር በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለማገልገል ዝግጁዎች ሆኑ። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ኻያ አምስት ዓመት የሞላውና ከዚያም በላይ የሆነ ሌዋዊ ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አገልግሎቱን ይፈጽማል፤ ኀምሳ ዓመት ሲሞላላቸው የአገልግሎት ሥራቸውን ይተዋሉ፤ ከዚያም በኋላ አይሠሩም። ከዚያ በኋላ ወንድሞቻቸው ሌዋውያን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለሚፈጽሙት አገልግሎት እንደ ረዳት ሆነው ይሠራሉ፤ እነርሱ ራሳቸው ብቻቸውን ግን ምንም ዐይነት ሥራ አይሥሩ፤ እንግዲህ የሌዋውያንን አገልግሎት ሥርዓት የምታስይዘው በዚህ ዐይነት ነው።”