እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “የጌርሾን ጐሣዎች የሆኑትን ሌዋውያን በየትውልዳቸውና በየቤተሰባቸው ቊጠራቸው፤ በመገናኛው ድንኳን ለማገልገል ብቃት ያላቸውን፥ ዕድሜአቸው ከሠላሳ እስከ ኀምሳ ዓመት የሆናቸውን ወንዶች ሁሉ ቊጠር፤ እነርሱ ልዩ ልዩ ዕቃዎችን የመሸከም ኀላፊነት ይኖራቸዋል። የመገናኛውን ድንኳን የውስጥና የውጪ መሸፈኛ፥ ከላይ የሚደረበውን የተለፋ ስስ ቊርበት፥ የመግቢያውን በር መጋረጃ ይሸከማሉ፤ እንዲሁም በድንኳኑና በመሠዊያው ዙሪያ ለሚገኘው አደባባይ የተሠሩትን መጋረጃዎችና አውታሮች፥ ለአደባባዩ መግቢያ በር የሚሆኑትን መጋረጃዎችና ለእነዚህ መገልገያ የተመደቡትን ሌሎችንም ዕቃዎች ሁሉ ይሸከማሉ፤ ለእነዚህም ዕቃዎች የሚሆነውን ማንኛውንም አገልግሎት ይፈጽማሉ። በሚሸከሙአቸው ነገሮችና በሚሠሩአቸው ሥራዎች የጌርሾንን ልጆች አገልግሎት አሮንና ልጆቹ ይቈጣጠሩአቸዋል፤ መሸከም ያለባቸውንም ነገሮች ሁሉ ትመድብላቸዋለህ። በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የጌርሾን ልጆች አገልግሎት ይህ ነው፤ ሥራቸውንም የካህኑ የአሮን ልጅ ኢታማር ይቈጣጠራል። “የሜራሪ ዘሮች የሆኑትን ሌዋውያን በየትውልዳቸው፥ በየቤተሰባቸው ቊጠራቸው፤ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለማገልገል ብቃት ያላቸውን፥ ዕድሜአቸው ከሠላሳ እስከ ኀምሳ ዓመት የሆናቸውን ወንዶች ሁሉ ቊጠር፤ እነርሱ መሸከም ያለባቸው ተራዳዎችን፥ መወርወሪያዎችን፥ ምሰሶችን፥ የማደሪያው ድንኳን የሚቆምባቸውን እግሮች፥ እንዲሁም በድንኳኑ ዙሪያ የሚገኘውን አደባባይ ምሰሶችን፥ እግሮቻቸውን፥ ካስማዎችን፥ አውታሮችንና ለእነዚህ ሁሉ መገልገያ የሆኑትን ዕቃዎች ነው፤ እያንዳንዱም መሸከም ያለበትን ዕቃ በየስሙ ትመድብለታለህ። በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታማር ተቈጣጣሪነት የሚካሄደው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሜራሪ ልጆች ቤተሰብ አገልግሎት ይህ ነው።” ሙሴ፥ አሮንና የሕዝቡ አለቆች የቀዓትን ዘሮች በየወገናቸው፥ በየቤተሰባቸው ቈጠሩአቸው፤ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ወደ አገልግሎት የገቡትን ሁሉ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ ኀምሳ ዓመት ያሉትን ቈጠሩአቸው፤ የተቈጠሩት ብዛታቸው ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ኀምሳ ነበር፤ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት በመገናኛው ድንኳን ያገለገሉትና ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው የቀዓት ቤተሰቦች ሁሉ እነዚህ ነበሩ። በየቤተሰባቸውና በየወገናቸው የተቈጠሩት የጌርሾን ልጆች፥ በመገናኛው ድንኳን ለማገልገል መግባት የቻሉ፥ ዕድሜአቸው ከሠላሳ እስከ ኀምሳ ዓመት የሚሆን ሁሉ፥ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሠላሳ ነበሩ። እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት በመገናኛው ድንኳን ያገለገሉትና ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው የጌርሾን ልጆች እነዚህ ናቸው። በየቤተሰባቸውና በየወገናቸው የተቈጠሩት የሜራሪ ልጆች፥ በመገናኛው ድንኳን ለማገልገል መግባት የቻሉ፥ ዕድሜአቸው ከሠላሳ እስከ ኀምሳ ዓመት የሚሆን ሁሉ ሦስት ሺህ ሁለት መቶ ነበር። እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት በመገናኛው ድንኳን ያገለገሉትና ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው የሜራሪ ልጆች እነዚህ ናቸው። ሙሴ አሮንና የእስራኤል አለቆች በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች የቈጠሩአቸው ሌዋውያን፥ ከሠላሳ ዓመት ጀምሮ እስከ ኀምሳ ዓመት ድረስ ያሉትና በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሥራውን ለመሥራት፥ ዕቃውን ለመሸከም የገቡት፥ ጠቅላላ ቊጥራቸው ስምንት ሺህ አምስት መቶ ሰማኒያ ነበር። በዚህም ዐይነት እያንዳንዱ ሰው እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ተቈጠረ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ለሙሴ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት እያንዳንዱ የማገልገልንና የመሸከምን ኀላፊነት ተቀበለ።
ኦሪት ዘኊልቊ 4 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘኊልቊ 4:21-49
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos