እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ጌድሶናውያንንም በየቤተ ሰባቸውና በየጐሣቸው ቍጠራቸው፤ ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት የሆናቸውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡትን ወንዶች ሁሉ ቍጠር። “የጌድሶናውያን የሥራና የሸክም አገልግሎታቸው ይህ ነው፤ እነርሱም የማደሪያውን መጋረጃዎች፣ የመገናኛውን ድንኳን፣ መደረቢያውንና በላዩ ላይ ያለውን የአቆስጣ ቍርበት፣ የመገናኛውን ድንኳን ደጃፍ መጋረጃዎች ይሸከሙ፤ እንዲሁም በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያሉትን የአደባባዩን መጋረጃዎች፣ የአደባባዩን ደጃፍ መጋረጃ፣ ገመዶችና ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች ሁሉ ይሸከሙ፤ በዚህም ያገልግሉ። የጌድሶናውያን አገልግሎት ሁሉ፣ ሸክምም ሆነ ሌላ ሥራ አሮንና ልጆቹ በሚሰጡት አመራር መሠረት ይሆናል። የሚሸከሙትን ሁሉ በኀላፊነት ታስረክቧቸዋላችሁ። እንግዲህ የጌድሶናውያን ጐሣዎች በመገናኛው ድንኳን የሚኖራቸው አገልግሎት ይህ ነው፤ ተግባራቸውም በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር አመራር ሥር ይሆናል። “ሜራሪያውያንን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰቦቻቸው ቍጠራቸው፤ እንዲሁም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡትን ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት የሆናቸውን ወንዶች ሁሉ ቍጠር። በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አገልግሎቶቻቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ተግባራቸው ይህ ነው፤ የማደሪያውን ሳንቃዎች፣ መወርወሪያዎች፣ ምሰሶዎችንና መቆሚያ እግሮቻቸውን፣ ይሸከማሉ፤ እንደዚሁም በአደባባዩ ዙሪያ ያሉትን ምሰሶዎች ከነመቆሚያ እግሮቻቸው፣ ካስማዎችን፣ ገመዶችን፣ ከእነዚሁ ጋር ያሉትን ዕቃዎች ሁሉና ማንኛውም ለአገልግሎቱ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ ይሸከማሉ። እያንዳንዱ ሰው የሚሸከመውን ዕቃ ለይታችሁ በስሙ መድቡለት። እንግዲህ የሜራሪያውያን ጐሣዎች በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር ሥር ሆነው በመገናኛው ድንኳን ሲሠሩ አገልግሎታቸው ይህ ነው።” ሙሴ፣ አሮንና የማኅበረ ሰቡ አለቆች ቀዓታውያንን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ቈጠሯቸው። ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት ሆኗቸው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለማገልገል የመጡት ወንዶች ሁሉ፣ በየጐሣቸው የተቈጠሩት ሁለት ሺሕ ሰባት መቶ አምሳ ነበሩ። ይህ ከቀዓት ጐሣዎች ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ያገለገሉት ሰዎች ጠቅላላ ድምር ነው። ሙሴና አሮን፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት እነዚህን ቈጠሯቸው። ጌድሶናውያን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ተቈጥረው ነበር። በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡት ከሠላሳ እስከ ሃምሳ ዓመት የሆናቸው ወንዶች ሁሉ፣ በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው የተቈጠሩት ሁለት ሺሕ ስድስት መቶ ሠላሣ ነበሩ። ይህ ከጌድሶን ጐሣዎች በመገናኛው ድንኳን ያገለገሉት ሰዎች ጠቅላላ ድምር ነው፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሙሴና አሮን እነዚህን ቈጠሯቸው። ሜራሪያውያንም በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ተቈጥረው ነበር። በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡት ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት የሆናቸው ወንዶች ሁሉ፣ በየጐሣቸው የተቈጠሩት ሦስት ሺሕ ሁለት መቶ ነበሩ። ይህ የሜራሪ ጐሣዎች ጠቅላላ ድምር ነው፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሙሴና አሮን እነዚህን ቈጠሯቸው። ስለዚህ ሙሴ፣ አሮንና የእስራኤል አለቆች ሌዋውያኑን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ቈጠሯቸው፤ ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት ሆኗቸው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አገልግሎት ለመስጠትና ለመሸከም የመጡት፣ ቍጥራቸው ስምንት ሺሕ አምስት መቶ ሰማንያ ነበሩ። እግዚአብሔር (ያህዌ) በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት እያንዳንዱ በየአገልግሎቱና በየሸክም ሥራው ተደለደለ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት ቈጠራቸው።
ዘኍል 4 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘኍል 4
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘኍል 4:21-49
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos