የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 4:1-20

ኦሪት ዘኊልቊ 4:1-20 አማ05

እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “ከሌዊ ልጆች መካከል የቀዓትን ዘር በየቤተሰባቸውና በየጐሣቸው ቊጠር፤ በመገናኛው ድንኳን ለማገልገል ብቃት ያላቸውን፥ ዕድሜአቸው ከሠላሳ እስከ ኀምሳ የሚደርሰውን ወንዶች ሁሉ መዝግብ። የእነርሱም አገልግሎት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚገኙትን ንዋያተ ቅድሳት መንከባከብ ይሆናል። “ሕዝቡ ከሰፈረበት ቦታ በሚነሣበት ጊዜ አሮንና ልጆቹ ወደ ድንኳኑ ገብተው፥ በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለፊት ያለውን መጋረጃ በማውረድ የኪዳኑን ታቦት በእርሱ ይጠቅልሉት። የተለፋውንም የቊርበት መሸፈኛ በመጋረጃው ላይ አድርገው በዚያም ላይ ሁለንተናው ሰማያዊ የሆነ መጐናጸፊያ ዘርግተው ያልብሱት፤ መሎጊያዎችንም ያስገቡ። “ለእግዚአብሔር የሚቀርበው የተቀደሰ ኅብስት ማኖሪያ የሆነውንም ገበታ በሰማያዊ ጨርቅ ይሸፍኑት፤ በገበታውም ላይ ሳሕኖችን፥ ጭልፋዎችን፥ ጽዋዎችንና የወይን ጠጅ መቅጃዎችን ያኑሩ፤ ኅብስትም ዘወትር በእርሱ ላይ ይኑርበት። ይህን ሁሉ በቀይ ጨርቅ ሸፍነው ከበላዩ የተለፋ ስስ ቊርበት ይደርቡ፤ መሎጊያዎችንም ያስገቡ። “ሰማያዊ ጨርቅ ወስደው መቅረዙን፥ ከነመብራቶቹ ከመኮስተሪያዎቹና ከኩስታሪ ማኖሪያዎቹ፥ እንዲሁም ከዘይት ዕቃዎቹ ሁሉ ጋር ይሸፍኑት። መቅረዙንና የእርሱን መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ በቈዳ መሸፈኛ ጠቅልለው በመሸከሚያ ተራዳ ላይ ያኑሩት። “ቀጥሎም የወርቁን መሠዊያ በሰማያዊ ጨርቅ ሸፍነው የተለፋ ስስ ቊርበት በላዩ ያድርጉ፤ መሎጊያዎችንም ያስገቡበት። በመቅደሱ መገልገያ የሆኑትን ዕቃዎች ሁሉ ወስደው በሰማያዊ ጨርቅ ይሸፍኑአቸው፤ የለፋ ስስ ቊርበት ደርበውም በመሸከሚያው ተራዳ ላይ ያኑሩአቸው። ዐመዱንም ከመሠዊያው ላይ ከጠረጉ በኋላ መሠዊያውን በሐምራዊ ጨርቅ ይሸፍኑት። በመሠዊያው ላይ ለማገልገል የሚጠቅሙትን ዕቃዎች፥ ማለትም ማንደጃዎችን፥ ሜንጦዎችን፥ መጫሪያዎችንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን ያስቀምጡበት፤ የተለፋውንም ስስ ቊርበት በላዩ ደርበው መሎጊያዎችን ያስገቡበት። ከሰፈር በሚነሡበትም ጊዜ አሮንና ልጆቹ ንዋያተ ቅድሳቱንና የእነርሱንም መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ ከሸፈኑ በኋላ የቀዓት ልጆች መጥተው ይሸከሙአቸው፤ ነገር ግን እንዳይሞቱ ንዋያተ ቅድሳቱን መንካት አይገባቸውም፤ እንግዲህ የመገናኛው ድንኳን በሚነሣበት ጊዜ ሁሉ የቀዓት ልጆች ኀላፊነት ይህ ነው። “የካህኑም የአሮን ልጅ አልዓዛር በመብራቱ ዘይት፥ ጣፋጭ ሽታ ባለው ዕጣን፥ ዘወትር በሚቀርበው በእህሉ ቊርባንና በቅባቱ ዘይት ላይ ኀላፊነት ይኖረዋል፤ እንዲሁም የመገናኛው ድንኳን በሙሉ፥ በእርሱም ውስጥ ያለውን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ዕቃ ሁሉ ይጠብቃል።” እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “የቀዓትን ልጆች ከሌዋውያን ነገድ መካከል ተቀሥፈው እንዲጠፉ አታድርጉ፤ ወደ ተቀደሰው ስፍራ ተጠግተው እንዳይሞቱ እንዲህ አድርግላቸው፦ አሮንና ልጆቹ ወደ መቅደሱ ገብተው የያንዳንዱን ሰው ሥራና ሸክሙን ይመድቡለት። ነገር ግን እንዳይሞቱ የቀዓት ልጆች ወደ ድንኳኑ ውስጥ ገብተው ለአንድ አፍታ እንኳ ለማየት አይድፈሩ።”