የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘኍል 4:1-20

ዘኍል 4:1-20 NASV

እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “ከሌዋውያን ወገን የቀዓት ዘር የሆኑትን በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው ቍጠሩ። እንዲሁም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ይሠሩ ዘንድ ለማገልገል የሚመጡትን ከሠላሳ እስከ አምሳ ዓመት የሆናቸውን ወንዶች ሁሉ ቍጠሩ። “በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የቀዓታውያን ሥራ ንዋየ ቅድሳቱን መጠበቅ ነው። ሰፈሩ ሲነሳ አሮንና ልጆቹ ገብተው የሚከልለውን መጋረጃ ያውርዱ፤ የምስክሩንም ታቦት ይጠቅልሉበት፤ ከዚያም በአቆስጣው ቍርበት ይሸፍኑት፤ ሙሉ በሙሉ ሰማያዊ የሆነ መጐናጸፊያ በላዩ ላይ ይዘርጉበት፤ መሎጊያዎቹንም በየቦታው ያስገቡ። “በገጸ ኅብስቱ ገበታ ላይ ሰማያዊ ጨርቅ ይዘርጉበት፤ በላዩም ላይ ወጭቶች፣ ጭልፋዎች፣ ጽዋዎች፣ ለመጠጥ ቍርባን የሚሆኑትን ማንቈርቈሪያዎች እንዲሁም ሁልጊዜ ከዚያ የማይታጣውን ኅብስት ያስቀምጡ። በእነዚህም ላይ ቀይ ጨርቅ ይዘርጉ፤ የአቆስጣውን ቍርበት ደርበውም መሎጊያዎቹን በየቦታቸው ያስገቡ። “ደግሞም ሰማያዊ ጨርቅ ወስደው ማብሪያ መቅረዙንና መብራቶቹን፣ መኮስተሪያዎቹንና የኵስታሪ መቀበያዎቹን፣ እንዲሁም ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉትን የዘይት ዕቃዎች ይሸፍኑበት። ከዚያም ይህንና ከዚሁ ጋር የተያያዙትን ዕቃዎች ሁሉ በአቆስጣ ቍርበት መሸፈኛ ጠቅልለው በመሸከሚያ ሳንቃ ላይ ያስቀምጡት። “በወርቅ መሠዊያ ላይ ሰማያዊ ጨርቅ ዘርግተው በአቆስጣ ቍርበት በመሸፈን መሎጊያዎቹን በየቦታቸው ያስገቡ። “እንዲሁም በመቅደሱ ውስጥ ለአገልግሎት የሚሆኑትን ዕቃዎች በሙሉ ወስደው በሰማያዊ ጨርቅ በአቆስጣ ቍርበት በመሸፈን በመሸከሚያው ሳንቃ ላይ ያስቀምጡት። “ከናሱ መሠዊያ ላይ ዐመዱን ጠርገው ሐምራዊ ጨርቅ ያልብሱት፤ ከዚያም ለመሠዊያው አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች በሙሉ፣ የእሳት ማንደጃዎቹን፣ ሜንጦዎቹን፣ የእሳት መጫሪያዎቹንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን በላዩ ላይ ያድርጉ፤ በእነዚህም ላይ የአቆስጣ ቍርበት መሸፈኛ አልብሰው መሎጊያዎቹን በየቦታቸው ያስገቡ። “አሮንና ልጆቹ መቅደሱንና ዕቃዎቹን፣ ንዋየ ቅድሳቱንም በሙሉ ሸፍነው ከጨረሱ በኋላ ሰፈሩ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ሲሆን፣ ቀዓታውያን ለመሸከም ይምጡ፤ እንዳይሞቱ ግን ንዋየ ቅድሳቱን መንካት የለባቸውም፤ ስለዚህ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ያሉትን እነዚህን ዕቃዎች የሚሸከሙ ቀዓታውያን ናቸው። “የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር በመብራቱ ዘይት፣ ደስ የሚያሰኝ ሽታ ባለው ዕጣን፣ ዘወትር በሚቀርበው በእህል ቍርባንና በቅብዐ ዘይቱ ላይ ኀላፊነት ይኖረዋል፤ እንደዚሁም ማደሪያውንና በውስጡ ያለውን ሁሉ መቅደሱንና ዕቃዎቹን ጭምር ይጠብቃል።” እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “የቀዓት ጐሣዎች ከሌዋውያን ተለይተው እንዳይጠፉ፤ ወደ ንዋየ ቅድሳቱ በሚቀርቡበትም ጊዜ በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ እንዳይሞቱ አንተ ይህን አድርግላቸው፤ አሮንና ልጆቹ ወደ መቅደሱ ይግቡ፤ እያንዳንዱንም ሰው በየሥራው ላይ ይደልድሉት፤ ምን መሸከም እንዳለበትም ያስታውቁት። ቀዓታውያን ግን ንዋየ ቅድሳቱን ለአንድ አፍታ እንኳ ለማየት አይግቡ፤ ቢገቡ ይሞታሉ።”