የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 27:1-11

ኦሪት ዘኊልቊ 27:1-11 አማ05

የሔፌር፥ የገለዓድ፥ የማኪር፥ የምናሴ፥ የዮሴፍ ልጅ የሆነው ጸሎፍሐድ፥ ማሕላ፥ ኖዓ፥ ሖግላ፥ ሚልካ እና ቲርጻ ተብለው የሚጠሩ ሴቶች ልጆች ነበሩት። እነርሱም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሄደው መላው ማኅበርና የሕዝቡ መሪዎች ባሉበት በሙሴና በአልዓዛር ፊት ቆመው እንዲህ አሉ፤ “አባታችን አንድ እንኳ ወንድ ልጅ ሳይወልድ በምድረ በዳ ሞተ፤ እርሱ በእግዚአብሔር ላይ ካመፁት ከቆሬ ተከታዮች ጋር ተባባሪ አልነበረም፤ የሞተውም በራሱ ኃጢአት ምክንያት ነው፤ ታዲያ፥ ወንድ ልጅ ባለመውለዱ ብቻ የአባታችን ስም ከእስራኤል ተፍቆ መጥፋት ይገባዋልን? ስለዚህ በአባታችን ዘመዶች መካከል ለእኛ የሚገባንን የርስት ድርሻ ስጡን።” ሙሴም የእነርሱን አቤቱታ ወደ እግዚአብሔር አቀረበ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “የጸሎፍሐድ ሴቶች ልጆች የጠየቁት ትክክል ነገር ነው፤ ስለዚህ በአባታቸው ዘመዶች መካከል ርስት ስጣቸው፤ የአባታቸው ድርሻ ወደ እነርሱ ይተላለፍ፤ ወንድ ልጅ ሳይወልድ የሚሞት ሰው ቢኖር ሴት ልጁ ንብረቱን መውረስ እንደሚገባት ለእስራኤል ሕዝብ አስታውቅ። ሴት ልጅም ከሌለው ወንድሞቹ ንብረቱን ይውረሱ፤ ወንድሞችም ከሌሉት የአባቱ ወንድሞች ይውረሱ፤ ወንድሞችም ሆኑ አጐቶች ከሌሉት የቅርብ ዘመዱ የሆነ ሰው ንብረቱን ወርሶ ሊጠቀምበት ይችላል፤ እኔ እግዚአብሔር ባዘዝኩህ መሠረት የእስራኤል ሕዝብ ይህን ሕግና ሥርዓት ቋሚ መመሪያ አድርገው ይጠብቁት።”