ሙሴ ለኤዶም ንጉሥ እንዲህ ብለው እንዲነግሩት መልእክተኞችን ከቃዴስ ላከ፤ “ወንድምህ እስራኤል እንዲህ ይላል፦ በእኛ ላይ የደረሰውን ችግር ሁሉ ሰምተሃል፤ የቀድሞ አባቶቻችን እንዴት ወደ ግብጽ እንደ ወረዱና እኛም በግብጽ ለብዙ ዓመቶች እንዴት እንደ ኖርን ታውቃለህ፤ ግብጻውያን የቀድሞ አባቶቻችንም ሆነ እኛን በብርቱ አሠቃይተዋል፤ እኛም ይረዳን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጮኽን፤ እርሱም ጩኸታችንን ሰምቶ ከግብጽ የሚያወጣንን መልአክ ላከልን፤ እነሆ አሁን እኛ በግዛትህ ወሰን ላይ ባለችው በቃዴስ እንገኛለን። ስለዚህ በምድርህ አልፈን እንድንሄድ እባክህ ፍቀድልን፤ እኛም ሆንን ከብቶቻችን ከመንገድ ውጪ አንወጣም፤ ወደ እርሻዎችህም ሆነ ወደ ወይን ተክሎችህ አንገባም፤ ከውሃ ጒድጓዶችህም አንጠጣም፤ ግዛትህን እስክናልፍ ድረስ ከዋናው መንገድ አንወጣም።” ኤዶማውያን ግን እንዲህ አሉ፤ “በአገራችን አልፋችሁ እንድትሄዱ አንፈቅድላችሁም! ለመግባት ብትሞክሩ ግን በሰልፍ ወጥተን እንወጋችኋለን።” የእስራኤል ሕዝብም “እኛ ከዋናው መንገድ አንወጣም፤ እኛ ወይም እንስሶቻችን ከውሃችሁ ብንጠጣ እንኳ ዋጋ እንከፍላችኋለን፤ እኛ የምንፈልገው በምድራችሁ አልፈን መሄድ ብቻ ነው” ሲሉ መለሱላቸው። ኤዶማውያን ግን “አይሆንም! አናሳልፋችሁም!” አሉ፤ ብርቱ የጦር ሠራዊትም አሰልፈው የእስራኤልን ሕዝብ ሊወጉ ወጡ። ኤዶማውያን እስራኤላውያን በግዛታቸው አልፈው እንዳይሄዱ በመከልከላቸው ምክንያት እስራኤላውያን መንገድ ለውጠው በሌላ በኩል ሄዱ። መላው የእስራኤል ማኅበር ከቃዴስ ተነሥተው በመጓዝ ወደ ሖር ተራራ ደረሱ፤ ይህም በኤዶም ወሰን ላይ የሚገኝ ስፍራ ነው፤ እዚያም እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “አሮን ለእስራኤላውያን ልሰጣቸው ቃል ወደገባሁላቸው ምድር አይገባም፤ እናንተ ሁለታችሁ በመሪባ ውሃ ዘንድ በትእዛዜ ላይ ስላመፃችሁ አሮን ይሞታል። አሮንንና ልጁን አልዓዛርን ይዘህ ወደ ሖር ተራራ ውጣ። እዚያም የአሮንን የክህነት ልብስ አውልቀህ አልዓዛርን አልብሰው፤ አሮንም በዚያ ይሞታል።” ሙሴም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ፤ መላው ማኅበር እየተመለከታቸው ወደ ሖር ተራራ ወጡ፤ ሙሴም የአሮንን የክህነት ልብስ አውልቆ አልዓዛርን አለበሰው፤ እዚያም በተራራው ጫፍ ላይ አሮን ሞተ፤ ሙሴና አልዓዛርም ተመልሰው ከተራራው ወረዱ፤ መላው ማኅበር አሮን እንደ ሞተ ሰሙ፤ እስከ ሠላሳ ቀንም ድረስ በሐዘን አለቀሱለት።
ኦሪት ዘኊልቊ 20 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘኊልቊ 20:14-29
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos