ሙሴ ከቃዴስ ለኤዶም ንጉሥ እንዲህ ሲል መልእክተኞች ላከ፤ “ወንድምህ እስራኤል የሚለው ይህ ነው፤ የደረሰብን መከራ ሁሉ ምን እንደ ሆነ አንተም ታውቃለህ። የቀድሞ አባቶቻችን ወደ ግብፅ ወረዱ፤ እኛም እዚያ ብዙ ዘመን ኖርን። ግብፃውያን እኛንም አባቶቻችንንም አሠቃዩን፤ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) በጮኽን ጊዜ ግን ጩኸታችንን ሰማ፤ መልአክ ልኮም ከግብፅ አወጣን። “አሁንም ያለነው እዚሁ ቃዴስ በግዛትህ ድንበር ላይ ባለችው ከተማ ነው። ስለዚህ በአገርህ እንድናልፍ እባክህን ፍቀድልን፤ በየትኛውም ዕርሻ ወይም የወይን ተክል ውስጥ አንገባም፤ ከየትኛውም ጕድጓድ ውሃ አንጠጣም። የንጉሡን አውራ ጐዳና ይዘን ከመጓዝ በስተቀር፣ ግዛትህን ዐልፈን እስክንሄድ ድረስ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አንልም።” ኤዶም ግን እንዲህ ሲል መለሰ፤ “በዚህ በኩል አታልፉም፤ እናልፋለን የምትሉ ከሆነ በሰልፍ ወጥተን በሰይፍ እንመታችኋለን።” እስራኤላውያንም መልሰው፣ “አውራውን መንገድ ይዘን እንሄዳለን፤ እኛም ሆንን ከብቶቻችን የትኛውንም ውሃችሁን ከጠጣን ዋጋውን እንከፍላለን፤ በእግር ዐልፈን መሄድ ብቻ እንጂ ሌላ ምንም አንፈልግም።” አሏቸው። ኤዶምም እንደ ገና፣ “በዚህ ማለፍ አትችሉም” የሚል መልስ ሰጣቸው። ከዚያም ኤዶም ብዙና ኀይለኛ የሆነ ሰራዊት አሰልፎ ሊወጋቸው ወጣ፤ ስለዚህ ኤዶም በግዛቱ ዐልፈው እንዳይሄዱ ስለ ከለከላቸው እስራኤላውያን ተመለሱ። መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብ ከቃዴስ ተነሥቶ ወደ ሖር ተራራ መጣ። እግዚአብሔርም (ያህዌ) በኤዶም ወሰን አጠገብ ባለው በሖር ተራራ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “አሮን ወደ ወገኖቹ ይሰበሰባል፤ ሁለታችሁም በመሪባ ውሃ በትእዛዜ ላይ ዐምፃችኋልና ለእስራኤላውያን ወደምሰጣት ምድር አይገባም። አሮንንና ልጁን አልዓዛርን ወደ ሖር ተራራ ይዘሃቸው ውጣ። አሮን ወደ ወገኖቹ ስለሚሰበሰብ ልብሱን አውልቀህ ልጁን አልዓዛርን አልብሰው፤ አሮንም እዚያው ይሞታል።” ሙሴ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው አደረገ፤ መላው ማኅበረ ሰብ እያያቸው ወደ ሖር ተራራ ወጡ። ሙሴም የአሮንን ልብስ አውልቆ ልጁን አልዓዛርን አለበሰው፤ አሮንም እዚያው ተራራው ጫፍ ላይ ሞተ። ከዚያም ሙሴና አልዓዛር ከተራራው ወረዱ፤ መላው ማኅበረ ሰብም አሮን መሞቱን በተረዳ ጊዜ፣ የእስራኤል ቤት በሙሉ ሠላሳ ቀን አለቀሰለት።
ዘኍል 20 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘኍል 20
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘኍል 20:14-29
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos