የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 2:10-34

ኦሪት ዘኊልቊ 2:10-34 አማ05

በስተ ደቡብ በኩል በሮቤል ክፍል ዓርማ ሥር በየቡድናቸው ይሰፍራሉ፤ የሮቤል ነገድ መሪ የሸዴኡር ልጅ ኤሊጹር ነው፤ የእነርሱም ብዛት አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበር። በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩት የስምዖን ልጆች ይሆናሉ፤ የስምዖን ነገድ መሪ የጹሪሻዳይ ልጅ ሸሉሚኤል ነው፤ የእነርሱም ብዛት ኀምሳ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ነበር። ከዚያም የጋድ ነገድ ይቀጥላል፤ የጋድ ነገድ መሪ የደዑኤል ልጅ ኤልያሳፍ ነው፤ የእነርሱም ብዛት አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ ኀምሳ ነበር። እንደየክፍላቸው በሮቤል ሰፈር እንዲሰፍሩ የተደረጉት ሰዎች ብዛት አንድ መቶ ኀምሳ አንድ ሺህ አራት መቶ ኀምሳ ነበር። በዚህ ዐይነት የሮቤል ክፍል ሁለተኛ ተራ ተጓዥ ይሆናል። በመጀመሪያዎቹ ሁለት ክፍሎችና በመጨረሻዎቹ ሁለት ክፍሎች መካከል ሌዋውያን የመገናኛውን ድንኳን ይዘው ይጓዛሉ፤ እያንዳንዱም ክፍል ሰፈሩ ተለይቶ በሚታወቅበት ዓርማ ሥር ምድብ ተራውን ጠብቆ ይጓዛል። በስተምዕራብ በኩል በኤፍሬም ክፍል ዓርማ ሥር በየቡድናቸው ይሰፍራሉ፤ የኤፍሬም ነገድ መሪ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሻማዕ ነው፤ የእነርሱም ብዛት አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበር። በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩት የምናሴ ልጆች ይሆናሉ፤ የምናሴ ነገድ መሪ የጴዳጹር ልጅ ገማልኤል ነው፤ የእነርሱም ብዛት ሠላሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበር፤ ከዚያም የብንያም ነገድ ይቀጥላል፤ የብንያም ነገድ መሪ የጊድዖን ልጅ አቢዳን ነበር፤ የእነርሱም ብዛት ሠላሳ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበር። እንደየክፍላቸው በኤፍሬም ሰፈር እንዲሰፍሩ የተደረጉት ሰዎች ብዛት አንድ መቶ ስምንት ሺህ አንድ መቶ ነበር። በዚህ ዐይነት የኤፍሬም ክፍል ሦስተኛ ተራ ተጓዥ ይሆናል። በስተ ሰሜን በኩል በዳን ክፍል ዓርማ ሥር የሚሰፍሩ ወገኖች ናቸው፤ የዳን ነገድ መሪ የዓሚሻዳይ ልጅ አሒዔዜር ነው፤ ብዛታቸውም ሥልሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበር። በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩት የአሴር ልጆች ይሆናሉ፤ የአሴር ነገድ መሪ የዖክሪን ልጅ ፋግዒኤል ነው፤ የእነርሱም ብዛት አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ነበር። ከዚያም የንፍታሌም ነገድ ይቀጥላል፤ የንፍታሌም ነገድ መሪ የዔናን ልጅ አሒራዕ ነው፤ የእነርሱም ብዛት ኃምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበር። እንደየክፍላቸው በዳን ሰፈር እንዲሰፍሩ የተደረጉት ሰዎች ብዛት አንድ መቶ ኀምሳ ሰባት ሺህ ስድስት መቶ ነበር። በዚህ ዐይነት የዳን ክፍል የመጨረሻ ተራ ተጓዥ ይሆናል። እስራኤላውያን በየነገዳቸውና በየክፍላቸው የተቈጠሩት ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ ኀምሳ ነበር። ሌዋውያን ግን እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት፥ ከሌሎቹ የእስራኤል ሕዝብ ጋር አልተቈጠሩም። በዚህ ዐይነት የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት አደረጉ፤ እያንዳንዱ ነገድ ዓርማውን በመከተል ይሰፍር ነበር፤ እያንዳንዱም በየቤተሰቡ ተመድቦ ይጓዝ ነበር።