መጽሐፈ ነህምያ 9:1-37

መጽሐፈ ነህምያ 9:1-37 አማ05

በዚሁ ወር በሃያ አራተኛው ቀን የእስራኤል ሕዝብ በአንድነት ተሰበሰቡ፤ ስለ ኃጢአታቸው መጸጸታቸውንና ማዘናቸውን ለመግለጥም ማቅ ለብሰው፥ በራሳቸው ላይ ትቢያ ነስንሰው ጾሙ፤ ራሳቸውንም ከባዕዳን ሕዝቦች ሁሉ ለዩ፤ ከዚህም በኋላ ሁሉም ተነሥተው በመቆም፥ እነርሱና የቀድሞ አባቶቻቸው የሠሩትን ኃጢአት ሁሉ ተናዘዙ። እዚያው እንደ ቆሙም፥ የአምላካቸው የእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ሦስት ሰዓት ሙሉ ተነበበላቸው፤ ሌላም ሦስት ሰዓት ኃጢአታቸውን በመናዘዝ፥ ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር ሰገዱ። ለሌዋውያኑ መቆሚያ መድረክ ነበር፤ በዚያም ላይ ኢያሱ፥ ባኒ፥ ቃድሚኤል፥ ሸባንያ፥ ቡኒ፥ ሼሬብያ፥ ባኒና ከናኒ በመቆም፥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ጸለዩ። ኢያሱ፥ ቃድሚኤል፥ ባኒ፥ ሐሸባንያ፥ ሼሬብያ፥ ሆዲያ፥ ሸባንያና ፐታሕያ ተብለው የሚጠሩት ሌዋውያን፦ “ተነሥታችሁ በመቆም ዘለዓለማዊውን አምላካችሁን እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ከምስጋናና ከበረከት ሁሉ በላይ፥ ከፍ ከፍ ይበል! በሉ” አሉአቸው። ከዚህም ሁሉ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ሲሉ ጸለዩ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፥ አምላክ አንተ ብቻ ነህ፤ ሰማያትን፥ የሰማያትንም ሰማያት ከነሠራዊታቸው፥ ምድርንና በእርስዋም ላይ የሚገኘውን ሁሉ፥ ባሕሮችንና በእነርሱም ውስጥ የሚገኙትን ሁሉ፥ ፈጠርክ፤ ለሁሉም ሕይወትን ሰጠሃቸው፤ የሰማይ ሠራዊት ይሰግዱልሃል። የባቢሎን ክፍል ከሆነችው ዑር፥ አብራምን መርጠህ ያመጣኸው፥ ስሙንም አብርሃም ያልከው፥ አንተ እግዚአብሔር አምላክ ነህ። እርሱም ለአንተ ታማኝ እንደ ሆነ ተመልክተህ፥ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳንን አደረግህ፤ ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ኢያቡሳውያንና ጌርጌሳውያን የሚኖሩባትንም የከነዓንን ምድር ለዘሮቹ መኖሪያ ርስት አድርገህ ልትሰጠው ቃል ገባህለት፤ አንተ ታማኝ ስለ ሆንክ ቃል ኪዳንህን አጽንተህ ጠብቀሃል። “አንተ የቀድሞ አባቶቻችን በግብጽ የደረሰባቸውን መከራ አየህ፤ ቀይ ባሕር አጠገብ ሆነው እንድትረዳቸው ያቀረቡትን ልመና ሰማህ። በግብጽ ንጉሥ ላይ በባለሥልጣኖቹና በምድሩ በሚኖሩትም ሕዝብ ሁሉ ላይ ድንቅ ተአምራትን ገልጠህ አሳየህ። ይህንንም ያደረግኸው የቀድሞ አባቶቻችን እንዴት እንደሚጨቈኑ በማየትህ ነው፤ ይህንንም በማድረግህ እስከ ዛሬ ድረስ ዝናህ የገነነ ሆኖአል። ባሕሩን በፊታቸው ለሁለት ከፈልክ፤ በደረቅ ምድርም ተሻገሩ፤ ድንጋይ ወደ ጥልቅ ባሕር እንደሚጣል፥ እነርሱን ያሳድዱ የነበሩትንም ወደ ጥልቁ ጣልካቸው። በቀን በደመና ዐምድ መራሃቸው፤ በሌሊትም መንገዳቸውን በእሳት ዐምድ አበራህላቸው። ወደ ሲና ተራራ ወርደህ ከሰማይ ሕዝብህን አነጋገርካቸው፤ ትክክለኛና ፍትሓዊ ሕግንና ሥርዓትን፥ መልካም የሆኑትን ደንቦችንና ትእዛዞችን ሰጠሃቸው። የተቀደሰውን ሰንበትህንም እንዲያውቁ አደረግሃቸው፤ በአገልጋይህም በሙሴ አማካይነት ትእዛዞችህን፥ ድንጋጌህንና ሕጎችህን ሰጠሃቸው። “በተራቡም ጊዜ ምግብን ከሰማይ ሰጠሃቸው፤ በተጠሙም ጊዜ ውሃን ከአለት አፈለቅህላቸው፤ ለእነርሱ ልትሰጣቸው ቃል የገባህላቸውንም ምድር በቊጥጥራቸው ሥር ያደርጉ ዘንድ አዘዝካቸው። ነገር ግን የቀድሞ አባቶቻችን ትዕቢተኞችና እልኸኞች ሆኑ፤ ትእዛዞችህንም አልጠበቁም፤ ታዛዦችም አልሆኑም። በመካከላቸው ያደረግኸውን ተአምራት ሁሉ ረሱ፤ እልኸኞችም ሆነው፤ ወደ ግብጹ ባርነታቸው እንዲመልሳቸው መሪ መረጡ። አንተ ግን በፍቅር የተሞላህ፥ ለቊጣ የዘገየህ፥ ይቅር ባይ፥ ቸርና መሐሪ አምላክ በመሆንህ አልተውካቸውም። በጥጃ አምሳል ለራሳቸው ጣዖትን ሠርተው፥ ‘ከግብጽ ምድር መርቶ ያወጣን አምላክ ይህ ነው!’ አሉ፤ በአንተ ላይም ከፍተኛ የስድብን ቃል እንኳ ተናገሩ፤ ምሕረትህም ታላቅ በመሆኑ በዚያ ምድረ በዳ ይጠፉ ዘንድ አልተውካቸውም፤ ነገር ግን የደመናው ዐምድ በቀን ይመራቸው ነበር፤ የእሳቱ ዐምድ በሌሊት ያበራላቸው ነበር። የሚያስተምራቸውን ቸር መንፈስህን ሰጠሃቸው፤ የሚመገቡትን መና፥ የሚጠጡትንም ውሃ ሰጠሃቸው። አርባ ዓመት ሙሉ በበረሓ ረዳሃቸው፤ ከሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ ምንም አላሳጣሃቸውም፤ ልብሳቸው አላለቀም፤ እግራቸው አላበጠም። “የአሕዛብን መንግሥታትና ነገሥታትን ድል ነሥተው፥ ከምድራቸው አዋሳኞች የሆኑትን ጠረፎች እንዲይዙ አደረግህ፤ ሲሖን የተባለ ንጉሥ ይገዛት የነበረችውን ሐሴቦን ተብላ የምትጠራውን ምድር፥ በድል አድራጊነት ያዙ፤ ዖግ የተባለው ንጉሥ ይገዛት የነበረችውንም የባሳንን ምድር ወረሱ። ብዛታቸው እንደ ሰማይ ከዋክብት የሆኑ ልጆችን ሰጠሃቸው፥ ለቀድሞ አባቶቻቸው ትሰጣቸው ዘንድ ቃል የገባህላቸውን ምድር፥ በድል አድራጊነት እንዲይዙ ፈቀድክላቸው። ልጆቻቸው የከነዓንን ምድር ድል አድርገው ያዙ፤ በዚያ ይኖሩ የነበሩትንም ሕዝብ በፊታቸው ሆነህ አንተ ድል ነሣህላቸው፤ በነገሥታትና በዚያች የከነዓን አገር ሕዝብ ላይ የፈለጉትን ሁሉ ያደርጉባቸው ዘንድ ኀይልን ሰጠሃቸው። የተመሸጉ ከተሞችንና፥ ለም የሆነችውን ምድር፤ በመልካም ነገር ሁሉ የተሟሉ ቤቶችን፥ የውሃ ጒድጐዶችንና የወይን ተክል ቦታዎችን የወይራና ብዙ የፍሬ ዛፎችን ወረሱ፤ በልተው በመጥገብም ሰውነታቸውን አወፈሩ፤ በቸርነትህ በሰጠሃቸው መልካም ነገር ሁሉ ተደሰቱ። “ነገር ግን እነርሱ በአንተ ላይ ዐምፀው ለቃልህ አንታዘዝም አሉ፤ ሕግህንም ላለመስማት ፊታቸውን መለሱ፤ በማስጠንቀቅ ወደ አንተ እንዲመለሱ ያስተማሩአቸውን ነቢያትህን ገደሉ፤ በየጊዜውም በአንተ ላይ ክፉ የስድብ ቃል ተናገሩ፤ ስለዚህም ጠላቶቻቸው እነርሱን ድል አድርገው ይገዙአቸው ዘንድ አሳልፈህ ሰጠሃቸው፤ እነርሱም አስጨነቁአቸው። በችግራቸውም ጊዜ ወደ አንተ ጮኹ፤ አንተም በሰማይ ሆነህ ሰማሃቸው፤ ከምሕረትህ ታላቅነት የተነሣ፥ ከጠላቶቻቸው የሚታደጉ መሪዎችን ላክህላቸው። ነገር ግን ሰላም ባገኙ ጊዜ እንደገና ኃጢአት ሠሩ፤ አንተም እንደገና ድል ለሚነሡ ጠላቶቻቸው ተውካቸው እነርሱም ገዙአቸው፤ ነገር ግን አንተ እንድትረዳቸው እንደገና በጠየቁ ጊዜ በሰማይ ሆነህ ሰማሃቸው፤ ከርኅራኄህም የተነሣ በየጊዜው ታደግኻቸው። እነርሱም ወደ ሕግህ እንዲመለሱ አስጠነቀቅኻቸው፤ በትዕቢታቸው ግን ትእዛዞችህን ናቁ፤ ቢፈጽሙአቸው ሕይወት በሚሰጡት ሕጎችህ ላይ ኃጢአት ሠሩ። በልበ ደንዳናነት ፊታቸውን አዞሩ፤ በእልኸኛነታቸውም እምቢተኞች ሆኑ። አንተም ለብዙ ዓመቶች ታገሥካቸው፤ ያስተምሩአቸውም ዘንድ ነቢያትን በመንፈስህ አስነሣህላቸው፤ ነገር ግን እነርሱ አላዳመጡም፤ ስለዚህም ለጐረቤት ሕዝቦች ድል እንዲነሡአቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። እንደገናም ከምሕረትህ ታላቅነት የተነሣ አልተውካቸውም፤ አንተ ቸርና ይቅር ባይ አምላክም ስለ ሆንክ አልደመሰስካቸውም። “ቃል ኪዳንህንና ዘለዓለማዊ ፍቅርህን የምትጠብቅ፥ ታላቁ፥ ኀያሉና አስፈሪው አምላካችን ሆይ! በእኛ፥ በንጉሦቻችን፥ በመሪዎቻችን፥ በካህኖቻችን፥ በነቢዮቻችን፥ በቅድመ አያቶቻችን፥ እንዲሁም በሕዝብህ ሁሉ ላይ፥ ከአሦር ነገሥታት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ የደረሰውን መከራ ሁሉ አስብ። እኛን ለመቅጣት ያደረግኸው ውሳኔ ትክክል ነው፤ እኛ በደል ብንሠራም፥ አንተ በታማኝነትህ እንደ ጸናህ ነህ። የቀድሞ አባቶቻችን፥ ንጉሦቻችን፥ መሪዎቻችንና ካህኖቻችን ሕግህን አልጠበቁም፤ የሰጠሃቸውን ትእዛዞች ማስጠንቀቂያዎች አላዳመጡም። መንግሥታቸው በሰጠሃቸው ቸርነት፥ በሰጠሃቸው ሰፊና ለም መሬት፥ ይደሰቱ በነበረ ጊዜ እንኳ፥ አንተን አላመለኩም፥ ከኃጢአታቸውም አልተመለሱም። ስለዚህም አንተ ለአባቶቻችን ፍሬዋን እንዲበሉና በመልካም ነገሮችም እንዲደሰቱ፥ በሰጠሃቸው ምድር ላይ እነሆ፥ ዛሬ እኛ ባሪያዎች ሆነናል። እኛም ኃጢአት በመሥራታችን ምክንያት ስላሳዘንክ፥ የምድሪቱንም በረከት በእኛ ላይ ገዢዎች አድርገህ ላስነሣሃቸው ነገሥታት ገቢ ይሆናል፤ እነርሱ በእኛና በእንስሶቻችን ላይ ደስ ያሰኛቸውን ነገር ሁሉ ይፈጽማሉ፤ ከዚህም የተነሣ፥ በታላቅ ጭንቀት ላይ እንገኛለን።”