መጽሐፈ ነህምያ 8:3-10

መጽሐፈ ነህምያ 8:3-10 አማ05

በዚያም አደባባይ ዕዝራ በቅጽሩ በር አጠገብ ቆሞ ከንጋት እስከ ቀትር የሕጉን መጽሐፍ ከፍ ባለ ድምፅ አነበበላቸው፤ ወንዶችም ሴቶችም ሁሉ በከፍተኛ ስሜት አዳመጡት። የሕግ ምሁሩ ዕዝራ ለዚሁ ተግባር አመች ይሆን ዘንድ ከዕንጨት በተሠራ መድረክ ላይ ቆሞ ነበር፤ ከእርሱም ጋር በስተቀኙ በኩል የቆሙት ሰዎች ማቲትያ፥ ሼማዕ፥ ዓናያ፥ ኡሪያ፥ ሒልቂያና መዕሤያ ሲሆኑ፥ በስተ ግራው በኩል ደግሞ ፐዳያ፥ ሚሻኤል፥ ማልኪያ፥ ሐሹም፥ ሐሽባዳናህ፥ ዘካርያስና መሹላም ቆመው ነበር። ዕዝራ ከሕዝቡ ከፍ ብሎ በተሠራው መድረክ ላይ በቆመ ጊዜ፥ ሁሉም ትኲር ብለው ይመለከቱት ነበር፤ እርሱም የሕጉን መጽሐፍ በከፈተ ጊዜ፥ ሁሉም ከተቀመጡበት ተነሡ፤ ዕዝራም ታላቁን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገነ። ሁሉም እጆቻቸውን ወደ ላይ በማንሣት “አሜን! አሜን!” ሲሉ መለሱ፤ ወደ ምድርም ለጥ ብለው ለእግዚአብሔር ሰገዱ። ከዚህ በኋላ ተነሥተው ባሉበት ስፍራ ቆሙ፤ ከዚህ ቀጥሎ ስማቸው የተዘረዘረ ሌዋውያንም የሕጉን መጽሐፍ ትርጒም ለሕዝቡ አብራሩላቸው፤ እነርሱም ኢያሱ፥ ባኒ፥ ሼሬብያ፥ ያሚን፥ ዓቁብ፥ ሻበታይ፥ ሆዲያ፥ መዕሤያ፥ ቀሊጣ፥ ዐዛርያስ፥ ዮዛባድ፥ ሐናንና ፐላያ ነበሩ። እነርሱም ለሕዝቡ የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አነበቡለት፤ ሕዝቡም የሚነበበው ይገባው ዘንድ ያብራሩለት ነበር። የሕጉን ቃል በሰሙ ጊዜ ሰዎቹ ስላለቀሱ፥ አገረ ገዢው ነህምያ፥ ካህኑና የሕግ ምሁሩ ዕዝራ፥ ሕዝቡን ያስተምሩ የነበሩት ሌዋውያን “ይህ ቀን ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ቀን ስለ ሆነ፥ አትዘኑ፤ አታልቅሱም” አሉአቸው። ነህምያ፦ “ሂዱና ምርጡን ምግብ ብሉ፤ ጣፋጩን መጠጥ ጠጡ፤ ምንም ለሌላቸውም ላኩ፤ ይህ ቀን ለአምላካችን የተቀደሰ ቀን ነው፤ የእግዚአብሔር ደስታ ኀይላችሁ ስለ ሆነ አትዘኑ” አላቸው።