መጽሐፈ ነህምያ 3:1-32

መጽሐፈ ነህምያ 3:1-32 አማ05

የከተማይቱ ቅጽር እንደገና የተሠራው በዚህ ዐይነት ነበር፦ ሊቀ ካህናቱ ኤልያሺብና የእርሱ ሥራ ባልደረቦች የሆኑት ካህናት “የበጎች በር” ተብሎ የሚጠራውን ቅጽር በር እንደገና ሠርተው ለእግዚአብሔር የተለየ አደረጉት፤ በሮችንም አበጁለት፤ ቅጽሩንም “መቶ” ተብሎ እስከሚጠራው የመጠበቂያ ግንብና “ሐናንኤል” ተብሎ እስከሚጠራው ሌላ የመጠበቂያ ግንብ ድረስ ለእግዚአብሔር የተለየ አደረጉት። የኢያሪኮ ሰዎች የዚያን ተከታይ ክፍል ሲሠሩ፥ ዘኩር የተባለው የኢምሪ ልጅ ከዚያ ቀጥሎ የሚገኘውን ክፍል ሠራ። የሃስናአ ጐሣ አባሎች የዓሣ ቅጽር በር የተባለውን ሠሩ፤ ምሰሶዎችንም አቆሙለት፤ በሮችንም ገጠሙ፤ ለበሮቹም መዝጊያ፥ መወርወሪያና ቊልፎችን አበጁ። የሀቆጽ የልጅ ልጅ የሆነው የኡሪያ ልጅ መሬሞት ከዚያ ቀጥሎ ያለውን ክፍል ሠራ። (አደሰ ቢሆን ይመረጣል) የመሼዛቤል የልጅ ልጅ የሆነው የበራክያ ልጅ መሹላም ቀጥሎ ያለውን ክፍል ሠራ፤ ከዚያም ቀጥሎ የሚገኘውን ክፍል የበዓና ልጅ ሳዶቅ ሠራው። (አደሰ ቢሆን ይመረጣል) የተቆዓ ከተማ ሰዎች ከዚያ ቀጥሎ ያለውን ክፍል ሠሩ፤ ነገር ግን የከተማይቱ ሹማምንት በተቈጣጣሪዎች የተመደበላቸውን የጒልበት ሥራ መሥራትን እምቢ አሉ። የፓሴሕ ልጅ ዮዳሄ፥ የበሶድያ ልጅ መሹላም የይሻናን ቅጽር በር ሠሩ፤ ምሰሶዎችንም አቆሙለት፤ በሮችንም ገጠሙ፤ ለበሮቹም ቊልፎችንና መወርወሪያዎችን አበጁ። የገባዖን ተወላጅ የሆነው መላጥያ፥ የሜሮኖት ተወላጅ የሆነው ያዶንና የገባዖንና የምጽጳ ሰዎች የኤፍራጥስ ምዕራብ አገረ ገዢ እስከሚኖርበት ቤት ድረስ ያለውን ክፍል ሠሩ። ወርቅ አንጣሪው የሐርሃያ ልጅ ዑዝኤል ከዚያ ቀጥሎ ያለውን ክፍል ሠራ። ቀጥሎ ያለውንም ክፍል ሽቶ ቀማሚው ሐናንያ ሠራ፤ እነዚህ ሰዎች ኢየሩሳሌምን “ሰፊው ቅጽር” ተብሎ እስከሚጠራው ስፍራ ድረስ ያለውን ሁሉ ሠሩ። ከእነርሱም ቀጥሎ ያለውን ክፍል የኢየሩሳሌም ወረዳ እኩሌታ ገዢ የሆነው የሑር ልጅ ረፋያ ሠራ። የሐሩማፍ ልጅ የዳያ ከቤቱ ፊት ለፊት የሚገኘውን ክፍል ሠራ። ቀጥሎ ያለውንም ክፍል የሐሻበንያ ልጅ ሐቱሽ ሠራው። የሓሪም ልጅ ማልኪያና የፓሐትሞአብ ልጅ ሐሹብ ከዚያ ቀጥሎ ያለውን ክፍልና “የእቶን ግንብ” ተብሎ የሚጠራውን ግንብ ሠሩ። ቀጥሎ ያለውንም ክፍል የሌላው የኢየሩሳሌም ወረዳ እኩሌታ ገዢ የሆነው የሀሎሔሽ ልጅ ሻሉም ሠራ፤ ሴቶች ልጆቹም ሥራውን ይረዱት ነበር። ሐኑንና የዛኖሐ ነዋሪዎች ተባብረው የሸለቆውን ቅጽር በር በማደስ ሠሩ፤ ለቅጽር በሩም መዝጊያዎችን አቁመው ቊልፎችንና መወርወሪያዎችን አበጁለት፤ እስከ ጒድፍ መጣያ ቅጽር በር 440 ሜትር ርዝመት ያለውንም ቅጽር እንደገና ሠሩ። የቤትሀካሬም ወረዳ ገዢ የሆነው የሬካብ ልጅ ማልኪያ የጒድፍ መጣያውን ቅጽር በር በማደስ ሠራ፤ በሮችን ገጠመ፤ ለበሮቹም ቊልፎችንና መወርወሪያዎችን አበጀ። የምጽጳ ወረዳ ገዢ የሆነው የኮልሖዜ ልጅ ሻሉም የምንጩን ቅጽር በር እንደገና ሠራ፤ ክዳን ከሠራለትም በኋላ መዝጊያዎችን አቆመ፤ ለበሮቹም ቊልፎችንና መወርወሪያዎችን አበጀ፤ በሼላሕ ኩሬ ቅጥር በኩል ከቤተ መንግሥቱ የአትክልት ቦታ ጀምሮ ከዳዊት ከተማ ወደታች እስከሚያወርደው ደረጃ ድረስ ያለውን ክፍል እንደገና ሠራ። የቤትጹር አውራጃ እኩሌታ ገዢ የነበረው የዓዝቡቅ ልጅ ነህምያ እስከ ዳዊት መቃብር (ከዳዊት መቃብር ትይዩ ጀምሮ)፥ እስከ ኩሬ፤ እስከ ጀግኖች ሰፈር ድረስ ያለውን ክፍል ሠራ። በቅጽሩ ሥራ ተካፋዮች የነበሩት ሌዋውያን ስም ዝርዝር ከዚህ የሚከተለው ነው፦ የባኒ ልጅ ረሑም ከዚያ ቀጥሎ ያለውን ክፍል ሠራ። የቀዒላ ወረዳ እኩሌታ ገዢ የሆነው ሐሻብያ ወረዳውን በመወከል ቀጥሎ ያለውን ክፍል ሠራ። ከዚያም ቀጥሎ ያለውን ክፍል የሌላው የቀዒላ ወረዳ እኩሌታ ገዢ የሆነው የሔናዳድ ልጅ ባዋይ ሠራው። የምጽጳ ወረዳ ገዥ የሆነው የኢያሱ ልጅ ዔዜር በጦር መሣሪያው ግምጃ ቤት ፊት ለፊት ያለውን እስከ ቅጽሩ መመለሻ ማእዘን ድረስ ያለውን ሁሉ ሠራ። የዛባይ ልጅ ባሩክም እስከ ሊቀ ካህናቱ ኤልያሺብ ቤት መግቢያ በር ድረስ ያለውን ሠራ። የሀቆጽ የልጅ ልጅ የሆነው የኡሪያ ልጅ መሬሞት እስከ ኤልያሺብ ቤት መጨረሻ ያለውን ሠራ። ከዚያ ቀጥሎ ያለውን ቅጽር የሠሩ ካህናት ስም ዝርዝር ይህ ነው፦ በኢየሩሳሌም ዙሪያ የነበሩት ካህናት ከዚያ ቀጥሎ ያለውን ክፍል ሠሩ። ከእነርሱም ቀጥሎ ብንያምና ሐሹብ በመኖሪያ ቤቶቻቸው ፊት ለፊት ያለውን ክፍል ሠሩ። የዐናኒያ የልጅ ልጅ የሆነውም የመዕሤያ ልጅ ዐዛርያ በራሱ መኖሪያ ቤት አጠገብ ያለውን ክፍል ሠራ። የሔናዳድ ልጅ ቢኑይ ከዐዛርያ ቤት አንሥቶ እስከ ቅጽሩ ማእዘን ያለውን ሠራ። የዑዛይ ልጅ ፓላል ከቅጽሩ ማእዘንና በዘብ መጠበቂያው አደባባይ አጠገብ ከሚገኘው ከላይኛው ቤተ መንግሥት መጠበቂያ ግንብ ጀምሮ ያለውን ክፍል ሁሉ ሠራ። የፓርዖሽ ልጅ ፐዳያ ደግሞ በውሃው ቅጽር በር አጠገብ ወደምሥራቅ የሚያመለክተውን ስፍራና የቤተ መቅደሱን መጠበቂያ ግንብ ይኸውም የቤተ መቅደሱ ሠራተኞች በሚኖሩበት የከተማይቱ አንድ ክፍል በሆነው “ዖፌል” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ አጠገብ ያለውን ክፍል ሠራ። የተቆዓ ሰዎችም ከዚያ ቀጥለው ለሁለተኛ ጊዜ ለቤተ መቅደሱ መጠበቂያ ከተሠራው ከታላቁ ግንብ ፊት ለፊት ጀምሮ በዖፌል አጠገብ እስከሚገኘው ቅጽር ያለውን ሠሩ። ሌሎች ካህናትም እያንዳንዳቸው በየመኖሪያ ቤታቸው ፊት ለፊት ያለውን መስመር በመከተል ከፈረስ ቅጽር በር በስተሰሜን በኩል ያለውን ክፍል ሠሩ። የኢሜር ልጅ ሳዶቅ በመኖሪያ ቤቱ ፊት ለፊት ያለውን ሲሠራ የምሥራቅ ቅጽር በር ጠባቂው የሸካንያ ልጅ ሸማዕያ ከዚያ ቀጥሎ ያለውን ሠራ። የሼሌምያ ልጅ ሐናንያና የጻላፍ ስድስተኛ ልጅ ሐኑን ለሁለተኛ ጊዜ የተሰጣቸውን ድርሻ ሠሩ። የበራክያ ልጅ መሹላምም በመኖሪያ ቤቱ ፊት ለፊት በኩል ያለውን ሠራ። ወርቅ አንጥረኛው ማልኪያ ተከታዩን መስመር ከቅጽሩ ማእዘን ሰሜናዊ ምሥራቅ ጫፍ አጠገብ እስካለው መቈጣጠሪያ ቅጽር በር በኩል የቤተ መቅደሱ ሠራተኞችና ነጋዴዎች እስከሚገለገሉበት ስፍራ ድረስ ሠራ። ወርቅ አንጥረኞችና ነጋዴዎችም ከቅጽሩ ማእዘን ጀምሮ እስከ በጎች ቅጽር በር ያለውን የመጨረሻውን ክፍል ሠሩ።