ነህምያ 3:1-32

ነህምያ 3:1-32 NASV

ሊቀ ካህናቱ ኤልያሴብና ወንድሞቹ ካህናት ለሥራ ተነሡ፤ የበጎች በር የተባለውንም እንደ ገና ሠሩ። ቀደሱት፤ መዝጊያዎቹንም በየቦታቸው ላይ አቆሙ። መቶ ግንብ እስከሚባለው ግንብና ሐናንኤል ግንብ ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ሠርተው ቀደሱት፤ ቀጥሎ ያለውንም የኢያሪኮ ሰዎች ሠሩ፤ እነርሱ ከሠሩት ቀጥሎ ደግሞ የአምሪ ልጅ ዛኩር ሠራ። የዓሣ በሩን የሃስናአ ልጆች ሠሩ፤ እነርሱም ምሰሶዎቹን አቁመው መዝጊያዎቹን፣ መቀርቀሪያዎቹንና መወርወሪያዎቹን በየቦታቸው አኖሩ። የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት ከዚያ ቀጥሎ ያለውን ክፍል መልሶ ሠራ። ከርሱ ቀጥሎ ያለውን የሜሴዜቤል ልጅ የቤራክያ ልጅ ሜሱላም መልሶ ሠራ። ከርሱ ቀጥሎ ያለውን የበዓና ልጅ ሳዶቅ መልሶ ሠራ፤ የሚቀጥለውን ክፍል የቴቁሔ ሰዎች መልሰው ሠሩ፤ መኳንንታቸው ግን በተቈጣጣሪ አሠሪዎቻቸው ሥር ሆነው በሥራው መጠመድ አልፈለጉም። አሮጌውን በር የፋሴሐ ልጅ ዮዳሄና የበሶድያ ልጅ ሜሱላም መልሰው ሠሩ፤ እነርሱም ምሰሶዎቹን አቁመው መዝጊያዎቹን፣ ማያያዣዎቹንና መወርወሪያዎቹን በየቦታቸው አኖሩ። ከእነርሱም ቀጥሎ የዕድሳቱ ሥራ የተከናወነው በኤፍራጥስ ማዶ በሚገኘው አገረ ገዥ ሥልጣን ሥር ባሉት በገባዖንና በምጽጳ ሰዎች በገባዖናዊው በመልጥያና በሜሮኖታዊው በያዶን ነበር። ከወርቅ አንጥረኞች አንዱ የሆነው የሐርሃያ ልጅ ዑዝኤል የሚቀጥለውን ክፍል ሠራ፤ ከሽቱ ቀማሚዎች አንዱ የሆነው ሐናንያ ደግሞ ከዚያ ቀጥሎ ያለውን መልሶ ሠራ። እነርሱም ሰፊው ቅጥር ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ኢየሩሳሌምን መልሰው ሠሩ። ከዚያ የሚቀጥለውን ክፍል የኢየሩሳሌም አውራጃ እኩሌታ ገዥ የሆነው የሑር ልጅ ረፋያ መልሶ ሠራ። የኤርማፍ ልጅ ይዳያ ከቤቱ ፊት ለፊት ያለውን ክፍል መልሶ ሠራ፤ የአሰበንያ ልጅ ሐጡስ ደግሞ ከርሱ ቀጥሎ ያለውን መልሶ ሠራ። የካሪም ልጅ መልክያና የፈሐት ሞዓብ ልጅ አሱብ ሌላውን ክፍልና የእቶን ግንብ ተብሎ የሚጠራውን መልሰው ሠሩ። የኢየሩሳሌም አውራጃ እኩሌታ ገዥ የሆነው የአሎኤስ ልጅ ሰሎም ከሴት ልጆቹ ጋራ በመሆን ቀጥሎ ያለውን ክፍል መልሶ ሠራ። “የሸለቆ በር” ተብሎ የሚጠራውን የሐኖንና የዛኖ ነዋሪዎች ዐደሱት፤ መልሰው ሠሩት፤ ከሠሩትም በኋላ መዝጊያዎቹን በየቦታቸው አኖሩ፤ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹንም አበጁ። እንዲሁም የቈሻሻ መጣያ በር ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ያለውን አንድ ሺሕ ክንድ ቅጥር መልሰው ሠሩ። የቈሻሻ መጣያ በር ተብሎ የሚጠራው የቤትሐካሪም አውራጃ ገዥ የሆነው የሬካብ ልጅ መልክያ መልሶ ሠራ፤ መልሶ ከሠራ በኋላም መዝጊያዎቹን፣ መቀርቀሪያዎቹንና መወርወሪያዎቹን በየቦታቸው አኖረ። የምጽጳ አውራጃ አለቃ የኮልሖዜ ልጅ ሰሎም “የምንጭ በር” ተብሎ የሚጠራውን መልሶ ሠራ፤ መልሶ ከሠራም በኋላ ከድኖ መዝጊያዎቹን በየቦታቸው አኖረ፤ መወርወሪያዎቹንና መቀርቀሪያዎቹንም አበጀ። የንጉሥ አትክልት ቦታ ተብሎ በሚጠራው አጠገብ የሚገኘውን የሼላን መዋኛ ግንብም፣ ከዳዊት ከተማ ጀምሮ ቍልቍል እስከሚወርደው ደረጃ ድረስ መልሶ ሠራ። ከርሱም በኋላ የቤትጹር አውራጃ እኩሌታ ገዥ የዓዝቡቅ ልጅ ነህምያ እስከ ዳዊት መቃብር ትይዩ እስከ ሰው ሠራሹ ኵሬና የጀግኖች ቤት ተብሎ እስከሚጠራው ድረስ ያለውን መልሶ ሠራ። ከርሱ ቀጥሎ ሌዋውያኑ በባኒ ልጅ በሬሁ ሥር ሆነው የዕድሳት ሥራ ሠሩ። ከርሱ ቀጥሎ የቅዒላ አውራጃ እኩሌታ ገዥ ሐሸብያ አውራጃውን መልሶ ሠራ። ከርሱ ቀጥሎ ያለውን ክፍል ደግሞ የሌላው የቅዒላ አውራጃ እኩሌታ ገዥ የኤንሐዳድ ልጅ በዋይና በርሱም ሥር የነበሩት የአገሩ ሰዎች መልሰው ሠሩ። ከርሱም ቀጥሎ ወደ ጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት በሚያወጣውና እስከ ማእዘኑ በሚደርሰው ትይዩ ያለውን ሌላ ክፍል የምጽጳ ገዥ የኢያሱ ልጅ ኤጽር መልሶ ሠራ። ከርሱም ቀጥሎ የዘካይ ልጅ ባሮክ ከማእዘኑ ጀምሮ እስከ ሊቀ ካህኑ እስከ ኤልያሴብ ቤት መግቢያ ያለውን ሌላ ክፍል በትጋት መልሶ ሠራ። ከርሱ ቀጥሎ ከኤልያሴብ ቤት መግቢያ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ያለውን ሌላ ክፍል የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት መልሶ ሠራ። ከርሱም ቀጥሎ ያለውን ክፍል ከአካባቢው የመጡት ካህናት መልሰው ሠሩ። ከእነርሱ ቀጥሎ ብንያምና አሱብ ከቤታቸው ፊት ለፊት ያለውን መልሰው ሠሩ፤ ከእነርሱም ቀጥሎ የሐናንያ ልጅ የመዕሤያ ልጅ ዓዛርያስ በቤቱ አጠገብ ያለውን መልሶ ሠራ። ከርሱም ቀጥሎ ከዓዛርያስ ቤት ጀምሮ እስከ ማእዘኑና እስከ ማእዘኑም ጫፍ ያለውን ሌላውን ክፍል የኤንሐዳድ ልጅ ቢንዊ መልሶ ሠራ፤ የኡዛይ ልጅ ፋላል ከቅጥሩ ማእዘን ትይዩና በዘብ መጠበቂያው አደባባይ አጠገብ ካለው ከላይኛው ቤተ መንግሥት መጠበቂያ ግንብ ጀምሮ ያለውን መልሶ ሠራ። ከርሱም ቀጥሎ የፋሮስ ልጅ ፈዳያና በዖፌል ኰረብታ ላይ የሚኖሩት የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች የውሃ በር ተብሎ ከሚጠራው ትይዩ ጀምሮ በስተምሥራቅ እስከሚገኘው ግንብ ድረስ መልሰው ሠሩ። ከእነርሱ ቀጥሎ የቴቁሔ ሰዎች ከታላቁ ግንብ ትይዩ ጀምሮ እስከ ዖፌል ቅጥር ድረስ ያለውን ሌላ ክፍል መልሰው ሠሩ። የፈረስ በር ተብሎ ከሚጠራው በላይ ያለውን ደግሞ ካህናቱ እያንዳንዳቸው በየመኖሪያ ቤታቸው ትይዩ ያለውን መልሰው ሠሩ። ከእነርሱም ቀጥሎ የኢሜር ልጅ ሳዶቅ በቤቱ ትይዩ ያለውን መልሶ ሠራ። ከርሱ ቀጥሎ ያለውን የምሥራቅ በር ጠባቂ የሆነው የሴኬንያ ልጅ ሸማያ መልሶ ሠራ። ከርሱ ቀጥሎ ያለውን ሌላ ክፍል ደግሞ የሰሌምያ ልጅ ሐናንያና የሴሌፍ ስድስተኛ ልጅ ሐኖን መልሰው ሠሩ። ከእነርሱም ቀጥሎ የቤራክያ ልጅ ሜሱላም ከመኖሪያው ትይዩ ያለውን መልሶ ሠራ። ከርሱ ቀጥሎ ከወርቅ አንጥረኞች አንዱ መልክያ በመቈጣጠሪያው በር ትይዩ እስከሚገኘው እስከ ቤተ መቅደሱ አገልጋዮችና እስከ ነጋዴዎቹ ቤት፣ እንዲሁም ከማእዘኑ በላይ እስከሚገኘው ክፍል ያለውን መልሶ ሠራ፤ ከማእዘኑ በላይ ከሚገኘው ክፍል ጀምሮ እስከ በጎች በር ያለውን ደግሞ ወርቅ አንጥረኞቹና ነጋዴዎቹ መልሰው ሠሩ።