አርጤክስስ በነገሠ በሃያኛው ዓመት ኒሳን ተብሎ በሚጠራው ወር ከዕለታት በአንዱ ቀን ለንጉሠ ነገሥቱ የወይን ጠጅ አቀረብኩለት፤ ከዚያች ቀን በቀር ከዚህ ቀደም በፊቴ ላይ ምንም ዐይነት የሐዘን ምልክት አይቶብኝ አያውቅም ነበር። ስለዚህም “አንዳች የልብ ሐዘን ቢደርስብህ ነው እንጂ ሳትታመም እንዴት ይህን ያኽል በፊትህ የሐዘን ምልክት ይታያል?” ሲል ጠየቀኝ። እኔም እጅግ በመፍራት፥ “ንጉሠ ነገሥቱ ለዘለዓለም ይኑር! የቀድሞ አባቶቼ የተቀበሩባት ከተማ ፍርስራሽ ሆና ስትቀርና የቅጽሮችዋም በሮች በእሳት ሲወድሙ እንዴት አላዝንም?” ስል መለስኩለት። ንጉሠ ነገሥቱም “ታዲያ፥ አሁን የምትፈልገው ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀኝ፤ እኔም ወደ ሰማይ አምላክ ከጸለይሁ በኋላ፥ ንጉሠ ነገሥቱን፦ “ንጉሥ ሆይ፥ በአንተ ፊት ሞገስን አግኝቼ ከሆነና ጥያቄዬን ከተቀበልከኝ፥ የቀድሞ አባቶቼ ወደተቀበሩባት በይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ እንድሄድና ከተማይቱን እንደገና መሥራት እንድችል ፍቀድልኝ” ብዬ ለመንኩት። በዚህን ጊዜ ንግሥቲቱ በንጉሠ ነገሥቱ አጠገብ ተቀምጣ ነበር፤ ንጉሠ ነገሥቱም ጥያቄዬን በመቀበል፦ “ጒዞህ ምን ያኽል ጊዜ ይወስድብሃል? እስከ መቼስ ትመለሳለህ?” ብሎ ጠየቀኝ። እኔም የሚወስድብኝን ጊዜና መቼ እንደምመለስ ነገርኩት። ከዚያም በመቀጠል ወደ ይሁዳ ማለፍ እንዲፈቅዱልኝ ከኤፍራጥስ ወንዝ በስተ ምዕራብ በሚገኘው ክፍለ ሀገር ላሉት አገረ ገዢዎች የይለፍ ደብዳቤ እንዲሰጠኝ ለንጉሠ ነገሥቱ ልመና አቀረብኩ፤ እንዲሁም አሳፍ የተባለው፥ የመንግሥት ደን ጠባቂ የሆነው፥ ለቤተ መቅደሱ ቅጽር በርና ለከተማይቱ ቅጽር በሮች ሁሉ እኔም ለማርፍበት ቤት ጭምር መጠበቂያዎች ማሠሪያ የሚሆን የጥድና የዝግባ እንጨት ለመቊረጥ እንዲፈቅድልኝ የሚያዝ ደብዳቤ እንዲሰጠኝም ጠየቅሁ፤ እግዚአብሔርም በቸርነቱ ስለ ረዳኝ፥ ንጉሠ ነገሥቱ የጠየቅሁትን ነገር ሁሉ ሰጠኝ። ንጉሠ ነገሥቱም ጥቂት የጦር መኰንኖችና ፈረሰኞች ከእኔ ጋር እንዲሄዱ አደረገ፤ እኔም ከኤፍራጥስ በስተ ምዕራብ ወደሚገኘው ክፍለ ሀገር ጒዞዬን ቀጠልኩ፤ እዚያ እንደ ደረስኩም ደብዳቤዎቹን ለአገረ ገዢዎቹ አስረከብኩ፤ ነገር ግን የቤትሖሮን ከተማ ነዋሪ የሆነው ሰንባላጥና የዐሞን ክፍለ ሀገር ባለሥልጣን የሆነው ጦቢያ ለእስራኤል ሕዝብ ደኅንነት መልካም ነገር የሚሠራ ሰው መምጣቱን ሰምተው እጅግ ተቈጡ። እኔም ወደ ኢየሩሳሌም ሄጄ ሦስት ቀን እዚያ ከቈየሁ በኋላ ለኢየሩሳሌም ስለማከናውነው ሥራ ሁሉ እግዚአብሔር ለእኔ የገለጠልኝን ምሥጢር ለማንም ሳልናገር ቈየሁ፤ ከዚያም በኋላ ከጓደኞቼ ጥቂቶቹን በማስከተል፥ በእኩለ ሌሊት ተነሥቼ ሄድኩ፤ የነበረን የጭነት እንስሳ እኔ የተቀመጥኩበት ብቻ ነበር፤ በሸለቆ ቅጽር በር ወጥቼ የዘንዶ ምንጭ ተብሎ የሚጠራውን ስፍራ በማለፍ፥ በስተ ደቡብ ወደሚገኘው የጒድፍ መጣያ ተብሎ ወደሚጠራው ስፍራ ሄድኩ፤ ጊዜውም ገና ሌሊት ነበር፤ በማልፍበትም ጊዜ የፈራረሱትን የከተማይቱን ቅጽሮችና በእሳት የወደሙትን የቅጽር በሮች ጐበኘሁ። ቀጥሎም ከከተማይቱ በስተ ምሥራቅ በኩል በሰሜን ወደሚገኘው “የውሃ ምንጭ ቅጽር በር” ተብሎ በሚጠራው ስፍራና ወደ ንጉሡ ኲሬ ሄድኩ፤ ነገር ግን ተቀምጬበት የነበረው እንስሳ የፍርስራሹን ክምር ለማለፍ የሚያስችለው መንገድ ማግኘት አልቻለም። ስለዚህ ሌሊቱን ወደ ቄድሮን ወንዝ በመውረድ፥ ቅጽሮችን እየጐበኘሁ አልፌ ሄድኩ፤ በመጨረሻም በዚያው በመጣሁበት መንገድ ተመልሼ በሸለቆው ቅጽር በር በኩል ወደ ከተማይቱ ገባሁ። በሀገሪቱ ከነበሩትም ባለሥልጣኖች መካከል የት እንደ ነበርኩና ምን እንዳደረግሁ ያወቀ ማንም አልነበረም፤ ከዚህም በቀር ከአይሁድ ጓደኞቼ ይኸውም ከካህናቱ፥ ከመሪዎቹም ሆነ ከባለሥልጣኖቹ ወይም የሥራው ተካፋዮች ከሚሆኑት ሌሎች ሰዎች ለአንዱም እንኳ የነገርኩት ምንም ነገር አልነበረም። ከዚህ በኋላ ግን “እንግዲህ ያለውን ችግር ሁሉ ተመልከቱት! ኢየሩሳሌም የፍርስራሽ ክምር ሆናለች፤ የቅጽር በሮችዋም በእሳት ወድመዋል፤ ስለዚህ ተነሥተን የከተማይቱን ቅጽሮች እንሥራ፤ የደረሰብንንም ኀፍረት እናስወግድ” አልኳቸው። ቀጠል አድርጌም እግዚአብሔር ከእኔ ጋር መሆኑንና እንዴትም እንደ ረዳኝ፥ ንጉሠ ነገሥቱም የነገረኝን ሁሉ ገለጥሁላቸው። እነርሱም “እንደገና መሥራቱን እንጀምር!” ካሉኝ በኋላ፥ ይህን በጎ ሥራ ለመጀመር ተዘጋጁ። ነገር ግን ሰንባላጥና ጦቢያ እንዲሁም ጌሼም ተብሎ የሚጠራው አንድ የዐረብ ተወላጅ እኛ ያወጣነውን የሥራ ዕቅድ በሰሙ ጊዜ በእኛ ላይ እየዘበቱ በመሳቅ “ይህ የምትሠሩት ሥራ ምንድን ነው? ወይስ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ ማመፅ ትፈልጋላችሁን?” ሲሉ ጠየቁን። እኔም “የሰማይ አምላክ ሥራችንን ለማከናወን ይረዳናል፤ እኛ የእርሱ አገልጋዮች ነን፤ ስለዚህም ሥራውን እንጀምራለን፤ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም ምንም ዐይነት ንብረት የማግኘት መብት ሆነ የታሪክ መታሰቢያነት አይኖራችሁም” ብዬ መለስኩላቸው።
መጽሐፈ ነህምያ 2 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ነህምያ 2:1-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች