የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ነህምያ 2:1-10

መጽሐፈ ነህምያ 2:1-10 አማ05

አርጤክስስ በነገሠ በሃያኛው ዓመት ኒሳን ተብሎ በሚጠራው ወር ከዕለታት በአንዱ ቀን ለንጉሠ ነገሥቱ የወይን ጠጅ አቀረብኩለት፤ ከዚያች ቀን በቀር ከዚህ ቀደም በፊቴ ላይ ምንም ዐይነት የሐዘን ምልክት አይቶብኝ አያውቅም ነበር። ስለዚህም “አንዳች የልብ ሐዘን ቢደርስብህ ነው እንጂ ሳትታመም እንዴት ይህን ያኽል በፊትህ የሐዘን ምልክት ይታያል?” ሲል ጠየቀኝ። እኔም እጅግ በመፍራት፥ “ንጉሠ ነገሥቱ ለዘለዓለም ይኑር! የቀድሞ አባቶቼ የተቀበሩባት ከተማ ፍርስራሽ ሆና ስትቀርና የቅጽሮችዋም በሮች በእሳት ሲወድሙ እንዴት አላዝንም?” ስል መለስኩለት። ንጉሠ ነገሥቱም “ታዲያ፥ አሁን የምትፈልገው ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀኝ፤ እኔም ወደ ሰማይ አምላክ ከጸለይሁ በኋላ፥ ንጉሠ ነገሥቱን፦ “ንጉሥ ሆይ፥ በአንተ ፊት ሞገስን አግኝቼ ከሆነና ጥያቄዬን ከተቀበልከኝ፥ የቀድሞ አባቶቼ ወደተቀበሩባት በይሁዳ ወደምትገኘው ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ እንድሄድና ከተማይቱን እንደገና መሥራት እንድችል ፍቀድልኝ” ብዬ ለመንኩት። በዚህን ጊዜ ንግሥቲቱ በንጉሠ ነገሥቱ አጠገብ ተቀምጣ ነበር፤ ንጉሠ ነገሥቱም ጥያቄዬን በመቀበል፦ “ጒዞህ ምን ያኽል ጊዜ ይወስድብሃል? እስከ መቼስ ትመለሳለህ?” ብሎ ጠየቀኝ። እኔም የሚወስድብኝን ጊዜና መቼ እንደምመለስ ነገርኩት። ከዚያም በመቀጠል ወደ ይሁዳ ማለፍ እንዲፈቅዱልኝ ከኤፍራጥስ ወንዝ በስተ ምዕራብ በሚገኘው ክፍለ ሀገር ላሉት አገረ ገዢዎች የይለፍ ደብዳቤ እንዲሰጠኝ ለንጉሠ ነገሥቱ ልመና አቀረብኩ፤ እንዲሁም አሳፍ የተባለው፥ የመንግሥት ደን ጠባቂ የሆነው፥ ለቤተ መቅደሱ ቅጽር በርና ለከተማይቱ ቅጽር በሮች ሁሉ እኔም ለማርፍበት ቤት ጭምር መጠበቂያዎች ማሠሪያ የሚሆን የጥድና የዝግባ እንጨት ለመቊረጥ እንዲፈቅድልኝ የሚያዝ ደብዳቤ እንዲሰጠኝም ጠየቅሁ፤ እግዚአብሔርም በቸርነቱ ስለ ረዳኝ፥ ንጉሠ ነገሥቱ የጠየቅሁትን ነገር ሁሉ ሰጠኝ። ንጉሠ ነገሥቱም ጥቂት የጦር መኰንኖችና ፈረሰኞች ከእኔ ጋር እንዲሄዱ አደረገ፤ እኔም ከኤፍራጥስ በስተ ምዕራብ ወደሚገኘው ክፍለ ሀገር ጒዞዬን ቀጠልኩ፤ እዚያ እንደ ደረስኩም ደብዳቤዎቹን ለአገረ ገዢዎቹ አስረከብኩ፤ ነገር ግን የቤትሖሮን ከተማ ነዋሪ የሆነው ሰንባላጥና የዐሞን ክፍለ ሀገር ባለሥልጣን የሆነው ጦቢያ ለእስራኤል ሕዝብ ደኅንነት መልካም ነገር የሚሠራ ሰው መምጣቱን ሰምተው እጅግ ተቈጡ።