በንጉሡ በአርጤክስስ ዘመነ መንግሥት በሃያኛው ዓመት ኒሳን ተብሎ በሚጠራው ወር የወይን ጠጅ በመጣለት ጊዜ፣ የወይን ጠጁን አንሥቼ ለንጉሡ ሰጠሁት። ቀድሞ በፊቱ ዐዝኜ አላውቅም ነበር፤ ስለዚህ ንጉሡ፣ “ሳትታመም ፊትህ ለምን እንዲህ ዐዘነ? መቼም ይህ የልብ ሐዘን እንጂ ሌላ አይደለም” አለኝ። እኔም በጣም ፈርቼ ነበር፤ ለንጉሡም “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር፤ አባቶቼ የተቀበሩባት ከተማ ስትፈርስ፣ በሮቿም በእሳት ሲቃጠሉ ለምን ፊቴ አይዘን?” አልሁት። ንጉሡም፣ “ታዲያ ምን ትፈልጋለህ?” አለኝ። ከዚያም ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይሁ፤ ለንጉሡም፣ “ንጉሡን ደስ የሚያሠኘው ቢሆንና ባሪያህ በፊትህ ሞገስ ቢያገኝ፣ እንደ ገና እንድሠራት አባቶቼ ወደ ተቀበሩባት ወደ ይሁዳ ከተማ እንድሄድ ይፈቀድልኝ” አልሁት። ከዚያም ንጉሡ አጠገቡ ከተቀመጠችው ንግሥት ጋራ በመሆን፣ “ጕዞህ ምን ያህል ቀን ይፈጃል? መቼስ ትመለሳለህ?” ሲል ጠየቀኝ። ንጉሡም እኔን ለመስደድ ደስ አለው፤ እኔም ጊዜውን ወሰንሁ። ደግሞም እንዲህ አልሁት፤ “ንጉሡን ደስ የሚያሠኘው ቢሆን፣ ይሁዳ እስክደርስ ድረስ በደኅና እንዲያሳልፉኝ ከኤፍራጥስ ማዶ ላሉት አገረ ገዦች ደብዳቤ ይሰጠኝ፤ እንዲሁም ለንጉሡ ደን ጠባቂ ለአሳፍ፣ በቤተ መቅደሱ አጠገብ ላለው ግንብ በሮች፣ ለከተማዪቱ ቅጥርና እኔም ለምገባበት ቤት ሠረገላ የሚሆን ዕንጨት እንዲሰጠኝ ደብዳቤ ይጻፍልኝ፤” መልካሚቱ የአምላኬ እጅ በእኔ ላይ ነበረችና ንጉሡም ፈቀደልኝ። ስለዚህ በኤፍራጥስ ማዶ ወደሚገኙት አገረ ገዦች ሄጄ የንጉሡን ደብዳቤዎች ሰጠኋቸው፤ ንጉሡም የጦር አለቆችና ፈረሰኞች ዐብረውኝ እንዲሄዱ አድርጎ ነበር። ሖሮናዊው ሰንባላጥና አሞናዊው ሹም ጦቢያ ይህን በሰሙ ጊዜ፣ ስለ እስራኤላውያን ደኅንነት የሚቈረቈር ሰው በመምጣቱ እጅግ ተበሳጩ።
ነህምያ 2 ያንብቡ
ያዳምጡ ነህምያ 2
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ነህምያ 2:1-10
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos