መጽሐፈ ነህምያ 1:1-10

መጽሐፈ ነህምያ 1:1-10 አማ05

የሐካልያ ልጅ ነህምያ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦ አርጤክስስ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት በሆነ በሃያኛው ዓመት ኪስሌው ተብሎ በሚጠራው ወር እኔ ነህምያ ዋና ከተማ በሆነችው በሱሳ ውስጥ ነበርኩ። ከወንድሞቼ አንዱ ሐናኒ ተብሎ የሚጠራው ሌሎች ሰዎችን አስከትሎ ከይሁዳ ወደ እኔ መጣ፤ እኔም ስለ ኢየሩሳሌምና ወደ ባቢሎን ተማርከው ከመወሰድ ስለ ተረፉትና በሕይወት ስላሉት አይሁድ ሁኔታ ጠየቅኋቸው። እነርሱም “ተማርከው ወደ ባቢሎን ሳይወሰዱ የቀሩትና በሕይወት ያሉት አይሁድ በታላቅ ችግርና ኀፍረት ላይ ወድቀው ይገኛሉ፤ የኢየሩሳሌምም ቅጽሮች ፈራርሰው ወድቀዋል፤ የቅጽር በሮቹም በእሳት ጋይተዋል” ሲሉ መለሱልኝ። እኔም ይህን ሁሉ በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስኩ። ለብዙ ቀኖችም በጾምና በሐዘን ቈየሁ፤ ወደ እግዚአብሔርም እንዲህ ስል ጸለይኩ፦ “እግዚአብሔር የሰማይ አምላክ ሆይ! አንተ ታላቅ ነህ፤ እኛም በፍርሃት በፊትህ እንቆማለን፤ አንተ ከሚወዱህና ትእዛዞችህንም ከሚጠብቁ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳንህን ትጠብቃለህ። እግዚአብሔር ሆይ! አገልጋዮችህ ስለ ሆኑት የእስራኤል ሕዝብ ደኅንነት ቀንና ሌሊት የማቀርበውን ጸሎቴን ስማ፤ እኔንም አስበኝ፤ እኛ እስራኤላውያን የሠራነውንም ኃጢአት እናዘዛለሁ፤ በእርግጥም እኔና የቀድሞ አባቶቼ በደል ሠርተናል። በአንተ ላይ በማመፅ ትእዛዞችህን ሁሉ ተላልፈናል፤ በአገልጋይህ በሙሴ አማካይነት የሰጠኸንንም ሕግና ሥርዓት አልጠበቅንም። ‘እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እኔን በእምነት ባትከተሉ በአረማውያን ሕዝቦች መካከል እበትናችኋለሁ፤ ነገር ግን ወደ እኔ ተመልሳችሁ ያዘዝኳችሁን ትእዛዞች ብትፈጽሙ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ የተበታተናችሁ ብትሆኑም እንኳ ለስሜ መጠሪያ እንዲሆን ወደ መረጥሁት ስፍራ እንደገና በመሰብሰብ መልሼ አመጣችኋለሁ’ ስትል ለሙሴ የተናገርከውን ቃል አስብ። “እግዚአብሔር ሆይ! እነዚህ የአንተ አገልጋዮችና የገዛ ሕዝብህ ናቸው፤ ከዚህ በፊትም በታላቁ ኀይልህና በብርቱ ክንድህ በመታደግ አድነሃቸዋል።