ነህምያ 1:1-10

ነህምያ 1:1-10 NASV

የሐካልያ ልጅ የነህምያ ቃል፤ በሃያኛው ዓመት ካሴሉ በተባለው ወር በሱሳ ግንብ ሳለሁ፣ ከወንድሞቼ አንዱ የሆነው አናኒ፣ ከሌሎች ጥቂት ሰዎች ጋራ ከይሁዳ መጣ፤ እኔም ከምርኮ ስለ ተረፉት የአይሁድ ቅሬታዎችና ስለ ኢየሩሳሌም ጠየቅኋቸው። እነርሱም፣ “በሕይወት ተርፈው ከምርኮ ወደ አገራቸው የተመለሱት ሰዎች በታላቅ መከራና ውርደት ላይ ይገኛሉ፤ የኢየሩሳሌም ቅጥር ፈራርሷል፤ በሮቿም በእሳት ተቃጥለዋል” አሉኝ። ይህን ነገር በሰማሁ ጊዜ አያሌ ቀናት ዐዘንሁ፤ ጾምሁ፤ በሰማይ አምላክም ፊት ጸለይሁ። ከዚያም እንዲህ አልሁ፤ “ለሚወድዱህና ትእዛዝህን ለሚያከብሩ የፍቅርህን ቃል ኪዳን የምትጠብቅ ታላቅና የተፈራህ አምላክ፣ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ባሪያህ ስለ አገልጋዮችህ ስለ እስራኤል ሕዝብ ቀንና ሌሊት በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎት ለመስማት ጆሮህ ይንቃ፤ ዐይንህም ይከፈት። እኔንና የአባቴን ቤት ጨምሮ እኛ እስራኤላውያን አንተን በመበደል የሠራነውን ኀጢአት እናዘዛለሁ። በአንተ ላይ እጅግ ክፉ ሥራ ሠርተናል፤ ለባሪያህም ለሙሴ የሰጠኸውን ትእዛዝ፣ ሥርዐትና ሕግ አልጠበቅንም። “ለባሪያህ ለሙሴ እንዲህ ስትል የሰጠኸውን ቃል ዐስብ፤ ‘ታማኞች ካልሆናችሁ፣ በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፤ ወደ እኔ ብትመለሱና ትእዛዞቼን ብትፈጽሙ፣ የተሰደዱት ወገኖቻችሁ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንኳ ቢበተኑ፣ ከዚያ እሰበስባቸዋለሁ፤ ለስሜም ማደሪያ ወደ መረጥሁት ስፍራ አመጣቸዋለሁ።’ “እነዚህም በታላቁ ኀይልህና በብርቱ እጅህ የተቤዠሃቸው ባሪያዎችህና ሕዝብህ ናቸው።